በትግራይ ጉዳይ በሱዳናዊቷ ጋዜጠኛ የተሰራውና አድሏዊው የሲኤንኤን ዘገባ ተቃውሞ

ጳጉሜ 5/2013 (ዋልታ) በትግራይ ክልል ወቅታዊ ጉዳይ በአሜሪካ መንግሥት የሚዘወረው ሲኤንኤን ያወጣው ዘገባ ፍፁም የተሳሳተ መሆኑን የዓለም ዐቀፉ የሳይበር ደኅንነት ስፔሻሊስትና የአሜሪካ የቀድሞው የመከላከያ መምሪያ ባልደረባ ኦሊቨር ቶማስ አስታወቁ።

አሜሪካዊው ኦሊቨር በቲውተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ከሲኤንኤን የወጣው ዘገባ ከዋሽንግተን አፀያፊ ፕሮፓጋንዳና ለአሸባሪው ሕወሓት ግልጽ የሆነ ድጋፍ የመነጨ ነው ብለዋል፡፡

ይልቁንም አሜሪካ ወራሪው ሕወሓት በአማራና አፋር የፈጸማቸውን አሰቃቂ የሆኑ ወንጀሎችን በመሸፈን የኢትዮጵያን መንግሥት በዘር ማጥፋት ወንጀል ልትከስ ይዳዳታል ነው ያሉት፡፡

በአሜሪካ የአፍሪካ የበላይ የመሆን ፍላጎት ምክንያት የተሰራው የሲኤንኤን ዘገባ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም አሜሪካዊው ሰው ግልፅ አድርገዋል፡፡

ዘገባው ሩሲያና ቻይና በአፍሪካ ትብብር ውስጥ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ቁርኝት በበጎ የማይመለከተው የዋሽንግተን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውጤት ስለመሆኑም ያነሳሉ፡፡

ዋናው ደግሞ የምርመራ ዘገባውን ሰራች የተባለችው ኒማ ኢልባጊር የተሰኘች ሱዳናዊት ጋዜጠኛ አገሯ በኅዳሴ ግድብ እና የድንበር ውዝግብ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ቅራኔ ሊታወስ ይገባል የሚሉት ኦሊቨር ቶማስ፤ ዘገባው የራስ ፍላጎት እንዳየለበት ማሳያ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህም ጋዜጠኛዋ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በገለልተኝነት ልትዘግብና መረጃን ልትመዝን አትችልምም ብለዋል፡፡

ምርመራ አደረኩ የሚለው ሲኤንኤን በሁመራ የጅምላ እስር፣ በእስር ቤት ማሰቃየትና ሰዎችን ማፈናቀል እንደተፈፀመና ለዚህም ተጠያቂው የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ ይገልፃል፡፡

ዋልታ እሁድ ይፋ ባደረገው ‹‹የዲጂታል ወያኔ አፈትላኪ የሃሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ዝግጅት›› ዘገባው በአሸባሪው ቡድን በኩል እየተደረገ ያለውን የሃሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ዝግጅትና ቀድሞ በሲኤንኤን የማሰራጨት፣ በዚህም ዓለም ዐቀፍ ጫና ለማሳደር መረባረብ በሚል እየተወሰደ ያለውን ስምሪት ቀድሞ ግልፅ ማድረጉ ይታወሳል፡፡