የርዕሰ መስተዳድሮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት

የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች

ጳጉሜ 5/2013 (ዋልታ) የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ለ2014 አድስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላለፉ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በመልዕክታቸው በልማት ስራ ላይ የነበረንን ተሳትፎ በአዲሱ ዓመትም አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም በርካታ ፈተናዎችን አስተናግደናል፤ ሆኖም በምክክርና በመግባባት ያቀድናቸውን በተባበረ ክንድ ማሳካት ችለናል ብለዋል፡፡

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በፈተናዎች ውስጥ የሰራናቸው ስራዎች አመርቂ ስለነበሩ በቀጣይም ያለአንዳች መዘናጋት በልማት ስራ ላይ የነበረንን ተሳትፎ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ በአዲሱ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫቸው፣ “አዲሱ 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ የምታሸንፍበት እና ድል የምትቀናጅበት ዓመት እንደሚሆን አምናለሁ፤ ጁንታው ከአማራ እና ከአፋር ክልል ብቻ ሳይሆን ከትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ጭምር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገዳል” ብለዋል።

በዚህም መላው ኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንዳቸውን አጠንክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስታውሰው፣ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር እና የብልፅግና እንድሆን ተመኝተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልለ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው አዲሱ ዓመት ከዚህ ቀደም ካጋጠሙን ፈተናዎች ወጥተን ስኬት ለማስመዝገብ በተለየ ትኩረት የምንሠራበት ነው ሲሉ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በርካታ የውጭና የውስጥ የጥፋት ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም በኢትዮጵያዊያን አንድነት ጥረታቸው የከሸፈበት ዓመት ነበር ብለዋል፡፡