ለ8ኛ ዙር የሚካሄደው የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት

መስከረም 04/2014 (ዋልታ) ስምንተኛው ዙር ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ስነሥርዓት መስከረም 8 እንደሚካሄድ ተገለጸ።
ሽልማቱ በጥራት የላቁና የአለም ገበያን መቆጣጠር የሚችሉ አምራቾችን እንዲሁም ተቋማትን ለማጎልበት ይረዳል ተብሏል።
ላለፉት ዓመታት 406 የሚሆኑ ድርጅቶችና ተቋማት በኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ውድድር መሳተፋቸው የተገለፀ ሲሆን፣ በዘንድሮ ዓመትም 42 ድርጅቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል። ውድድሩ በ7 ዘርፎች እንደሚከናወንም ድርጅቱ በሰጠው መግለጫ አመላክቷል።
ሽልማቱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶች ያላቸው ተቋማትን ለማጎልበት ያግዛል ነው የተባለው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጣሰው ወልደሃና (ፕ/ር) ጥራት ሲባል የደረጃ ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸው፣ ተቋማት በጥራት የተመረቱ ምርቶችን ተደራሽ ለማድረግ ተወዳዳሪነትን ለመጨመር የሚያግዝ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት በምስራቅ አፍሪካ በመማር ማስተማር ሂደት 1ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ተቀባይነትንና ተደራሽነትን ማግኘት የቻለው ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት አማካኝነት በ2000 ዓ.ም የተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው።
የሽልማት ስነሥርአቱ በታላቁ ቤተ መንግስት የሚከናወን ሲሆን፣ በዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት በቀጥታ ሥርጭት ይተላለፋል።
በሃኒ አበበ