ለመከላከያ ሰራዊቱ የ8 ሚሊየን ብር ድጋፍ

መስከረም 9/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ ለመከላከያ ሰራዊቱ 8 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡

ሼር ካምፓኒው በስሩ የሚገኙትን 18 የእግር ኳስ ቡድኖች በማስተባበር ነው ገንዘቡን የሰበሰበው፡፡

የርክክብ ስነሥርዓቱ  በመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች እና በታዋቂ አርቲስቶች መካከል በተካሄደው የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኤሳያስ ጅራ ጠላቶቻችን ሆነ ብለው ሀገርን የማፍረስ አጀንዳ ይዘው በሚንቀሳቀሱበት በዚህ ሰአት ከመበታተን ይልቅ አንድነት የተሻለ መሆኑን ለማረጋገጥ እግር ኳስ ታላቅ ማሳያ ነው ብለዋል።

የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ብርጋዴር ጄነራል አስፋው ማመጫ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያን በመታደግ ዘመቻ ላይ አርቲስቶች እና ስፖርተኞች በህዝብ ዘንድ  ያላቸውን ስም እና ዝና በመጠቀም ሀገር ፈተና ላይ በወደቀች ሰአት አለሁ በማለት ታላቅ አሻራ አሳርፈዋል ብለዋል።

የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ የመንግስት አካላትም ሆኑ ለጋሱ የኢትዮጵያ ህዝብ በራሳቸው ተነሳሽነት እያደረጉት የሚገኘት ጠንካራ ውግንና የሰራዊታችንን ተወዳጅነት የሚያሳይ ነው ሲሉ መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡