ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ በጋምቤላ ከተማ

መስከረም 9/2014 (ዋልታ) በጋምቤላ ከተማ በአንድ ባዶ ቤት ውስጥ 37 ክላሽንኮቭ እንዲሁም 3 የተለያዩ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ የጦር መሳሪዎቹን ትላንት በቁጥጥር ስር ማዋል የተቻለው በህብረተሰቡ ጥቆማ ፖሊስ ባደረገው ክትትል መሆኑን ገልጸዋል።

37ቱ የጦር መሳሪዎች የተገኙት በውሃ ሮቶ ምድር ውስጥ ተቀብረው እና 3ቱ ደግሞ ጫካ ውስጥ ተጥለው እንደሆነ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች መካከል 19 ታጣፊ ክላሽንኮቭ 18 ባለ ሠደፍ እና 3 የተለያዩ ጠብ መንጃዎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

መሳሪያዎቹን የደበቁ ግለሠቦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

በክልሉ እየተስፋፋ ያለውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለመግታት ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ ኮሚሽሩ ማሳሰባቸውን ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡