10 ሺሕ ተማሪዎችን በነፃ ለማስተማር የወሰነው የምስራቅ ጎጃም ዞን

መስከረም 10/2014 (ዋልታ) የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር አሸባሪው ትህነግ ከትምህርት ገበታ እንዲነጠሉ የወሰነባቸዉ 10 ሺሕ ተማሪዎች በነፃ ለማስተማር ወሰነ።

የትህነግ አሸባሪ ሃይል በፈጸመው ወረራና ጅምላ ጭፍጨፋ የጦርነቱ ሰለባ የሆኑ ተማሪዎችን በምስራቅ ጎጃም ዞን በሚገኙ ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች ተቀብሎ ለአንድ ዓመት በነፃ ለማስተማር ወስኗል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አያሌው አሸባሪው ቡድን በሰው ልጅ ህይወት ላይ ከፈጸመው አሰቃቂ እልቂት፣ በተቋማት ላይ ባደረሰው ውድመት ህጻናትን ያለአሳዳጊና ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆኑ አድርጓል ብለዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ህዝብ ጠላት በአማራነቱ የጥቃት ሰለባ ያደረገዉን የወሎን ህዝብ አጋርነቱን ለማሳየት በዞኑ ዉስጥ የሚገኙ 26 የገጠርና የከተሞች አስተዳደሮች 10 ሺሕ የችግሩ ሰለባ የሆኑ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለአንድ ዓመት ለማስተማር መወሰኑንም አስታውቀዋል።

የዞን አስተዳደሩ ተማሪዎችን ተቀብሎ በነፃ ለማስተማር የወሰነው ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎችን እንደሆነም ዋና አስተዳዳሪ ተናግረዋል።

የመምረጫ መመዘኛውም ወራሪው ቡድን በፈጸመው ግፍ ምክንያት ወላጆቻቸውን በሞት ያጡና ትምህርት ቤታቸው የፈረሰባቸውና ወላጆቻቸው ሌላ ቦታ ልከዉ ለማስተማር አቅም የሌላቸዉ ህፃናት ተማሪዎችን እንደሆነም አስተዳዳሪው አብራርተዋል።

ተማሪዎቹ ተመርጠው እንዲላኩላቸውም በነገዉ እለት ለአማራ ክልል ትምህርት ቢሮና ለሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ በድብዳቤ እንደሚጠይቁም አቶ አብርሃም ተናግረዋል።

ይህ ዉሳኔ የተወሰነዉ የዞንና የወረዳ አመራሮች ወቅታዊ የሥራ አፈፃፀሞች ዙሪያ በደብረማርቆስ ከተማ ዉይይት ካደረጉ በኋላ መሆኑን ከአማራ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።