በግለሰብ መኖሪያ ቤት በቁጥጥር ስር የዋለው 2 ሺህ 500 ተተኳሽ የሽጉጥ ጥይት

መስከረም 19/2014 (ዋልታ) በጎንደር ከተማ ከአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ተደብቆ የተቀመጠ 2 ሺህ 500 ተተኳሽ የሽጉጥ ጥይት ከአንድ ተጠርጣሪ ግለሰብ ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የከተማው ፖሊስ መምሪያ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር እየሩስ አስማረ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ ጥይቱ በቁጥጥር ስር የዋለው ዛሬ ረፋድ ላይ ከአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ተደብቆ  በህብረተሰቡ ጥቆማ  ነው፡፡

ህገ-ወጥ ጥይቱን መቆጣጠር የተቻለው ፖሊስ የፍርድ ቤት የፍተሻ ትእዛዝ በማውጣት በከተማው ማራኪ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 18 በሚገኘው የተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት ባደረገው ፍተሻ መሆኑንም ገልጸዋል።

“ፖሊስ የሕገ-ወጥ ጥይቱን ዋና ምንጭ ለማወቅ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር በማዋል በአሁኑ ወቅት ምርመራ በማድረግ ላይ ይገኛል” ብለዋል፡፡

ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያና ጥይት ዝውውር የዜጎችን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ወንጀል በመሆኑ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር የጀመረው የተቀናጀ ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ኢንስፔክተር እየሩስ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡