ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ አብዲሳ የሆራ ሃርሰዲ ኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ምስጋና አቀረቡ

መሰከረም 23/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የሆራ ሃርሰዲ ኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በርካታ ሰዎች የተገኙበት የሆራ ሃርሰዲ ኢሬቻ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላማዊ እና በተረጋጋ መንፈስ ተከብሮ መጠናቀቁ ኢሬቻ የምስጋና፣ የእርቅ፣ የፍቅር እና የይቅር ባይነት እንጂ ጥላቻ የሚሰበክበት እና የህቡዕ ፖለቲካ የሚራመድበት አለመሆኑን ያሳየ ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በሆራ ሃርሰዲ ኢሬቻ ላይ የታየው ጨዋነት የኦሮሞ ሕዝብ ክብርን እና ወግን ያንፀባረቀ መሆኑንም መግለጻቸውን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።
የኦሮሞ ሕዝብ ትላንት የኢሬቻን እሴቶች ከተፅዕኖ እና ከንክኪ ነፃ አድርጎ ለዛሬው ትውልድ እንዳበቃው ሁሉ እነዚህን እሴቶች በእንክብካቤ ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንደሚያሸጋግር ጥርጥር የለኝም ብለዋል አቶ ሽመልስ አብዲሳ።
የሆራ ሃርሰዲ ኢሬቻ በዓል እንደ ሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ሁሉ በማረ እና የኦሮሞን ማንነት በሚመዝን መልኩ እንዲከበር የአባ ገዳዎች እና የሀደ ሲንቄዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው በዓለም በሰላም እንዲከበር ላደረጋችሁ ቄሮዎች፣ ቀሬዎች እና ፎሌዎች ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላት በታላቅ ኃላፊነት የሕዝቡን ሰላም በማስጠበቅ እውነትም የሕዝቡ ጋሻ መሆናችሁን ስላስመሰከራችሁ ታላቅ ምስጋና ይድረሳችሁ ብለዋል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ።