የሽብርተኛውን ሃይል ለመደምሰስ ተዘጋጅተናል – የብርሸለቆ ምልምል ሰልጣኞች

መስከረም 23/2014 (ዋልታ) የብርሸለቆ መሰረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የ35ኛ ዙር ሰልጣኞች የስልጠና መክፈቻ ስነስርዓት ተከናውኗል።

በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ በመገኘት ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ዋና ኣዛዥ ኮለኔል ጌታቸው አሊ እኛ እያለን ሃገራችን አትደፈርም በማለት በአንድነት መንፈስ፣ በቁጭትና በሞራል በመነሳሳት ወኔና ጀግንንት ተላብሳችሁ የሀገራችን ታሪካዊ ጠላት የሆነውን የሽብርተኛ ቡድን በፅናት ለመፋለምና ግብዓተ መሬቱን ለመፈፀም የሚሰጣችሁን ስልጠና በአግባቡ በመወጣት የጠላትን አንገት በማስደፋት ለወገን መከታ፣ አለኝታና ኩራት መሆን አለባችሁ ብለዋል።
የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ምክትል አዛዥ ለስልጠና ሃላፊ ኮሎኔል ተዝገራ ከበደ በበኩላቸው፣ በማሰልጠኛ ቆይታችሁ የሚሰጣችሁን ወታደራዊ ስልጠና በብቃት መሰልጠን፣ በስልጠናው ሂደት የሚያጋጥማችሁን ጥቃቅን ችግሮች በቆራጥነት ማለፍና በጠንካራ ወታደራዊ ድስፕሊን ስልጠናውን በማጠናቀቅ ለህዝብና ለሃገር የገባችሁትን ቃል ልታረጋግጡ ይገባል ነው ያሉት።
አስተያየት የሰጡት ምልምል ሰልጣኞች ለሃገር ሉዓላዊነት ውድ ህይወቱን ከሚሰጠው ጀግና ሰራዊት ጎን ለመቆም ወደ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርቱ በመምጣታቸው መደሰታችውን ገልፀዋል።
የሚሰጣቸውን ወታደራዊ ስልጠና በቁርጠኝነት ሰልጥነው የሽብርተኛውን ኃይል ለመደምሰስ ዝግጁ መሆናቸውንም ምልምል ሰልጣኞቹ መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።