የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት በመንግስት የሥራ ሀላፊነት ውስጥ መካተታቸው በብዝሃ አተያይ አገርን ለመምራት ያስችላል ተባለ

መስከረም 23/2014 (ዋልታ) መንግስት የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን በአዲሱ የመንግስት መዋቅር ውስጥ በስራ ኃላፊነት ማካተቱ በብዝሃ አተያይ ሀገርን በአግባቡ መምራት እንደሚያስችል ምሁራን ገለጹ።

ምሁራኑ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ተፎካካሪዎችን ወደ መንግስት ስራ ኃላፊነት ማምጣቱ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል እንዲዳብር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲሱ የመንግስት መዋቅር ጅማሮ “አገር መምራት የአሸናፊ ፓርቲ ስልጣን ብቻ ነው” የሚለውን የተዛባ አመለካከት የቀየረ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እንዳለ ንጉሴ፤ ለአንድ አገር ብሔራዊ ጥቅም እና እድገት የሁሉም ዜጋ አስተዋጽኦና ተሳትፎ የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

“በየዘርፉ የበቃ እውቀት፣ አመለካከትና አስተሳሰብ ያላቸው ዜጎች ህዝብን የማገልገል እድሉን ሲያገኙ የተሻለች አገር መገንባት ይቻላል” ብለዋል።

በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት መካተታቸው በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ እየዳበረ የመምጣቱ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች የሚስተናገዱባትና የሃሳብ ብዝሃነት የሚከበርባት አገር መሆኗን በተግባር እንደሚያረጋግጥም ጠቅሰዋል፡፡

“የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካና የባህል እሴቶች መለያየት ቢኖርም በአገራዊ ጉዳይ ግን ኢትዮጵያዊያን በጋራ መቆም ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ መምህርና ተመራማሪ ንጉሱ በላይ (ዶ/ር) “ሂደቱ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ህዝብ የሰጠው ድምጽ ዋጋ እንዳለው የተረጋገጠበትና ምርጫው ፍትሃዊ መሆኑን የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

የህዝቦች፣ የፓርቲዎችና የመንግስት መተባበር በኢትዮጵያ የተሻሉ አማራጮች እንዲንጸባረቁ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በዋናነትም ”የተለያዩ ተሞክሮዎች፣ እውቀቶችና እሳቤዎች በአንድ ቋት ሲወጠኑ ለአገር እድገትና ብልጽግና ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል” ብለዋል።

በህዝቡ የሚነሱ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን በመለየት አፋጣኝ መፍትሄ ከመስጠት ባሻገር ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ጥሩ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ጀርመንና ህንድ በዘርፉ ስኬታማ ስራዎችን በማከናወን ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውንም በምሳሌነት አንስተዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2011 በህንድ በተካሄደ ምርጫ ድምጽ ያገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተካተው ፖሊሲያቸው እንዲተገበር ሆኗል።

በዚህም የአሸናፊው ፓርቲ እና እድሉን ያገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ባከናወኑት ፍሬያማ ስራ በህንድ የሚነሱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቅሬታዎች ምላሽ እያገኙ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።