የ10 ዓመቱን “ፍኖተ ብልጽግና” ለማሳካት የምክር ቤቱ ሚና የጎላ መሆኑ ተገለጸ

ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

መስከረም 27/2014 (ዋልታ) – የአስር ዓመቱን “ፍኖተ ብልጽግና” የልማት ዕቅድ ለማሳካት የምክር ቤት አባላት ሚና የጎላ መሆኑን የፕላን ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የፕላን ልማት ሚኒስቴር በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ኢትዮጵያ ለማሳካት ያስቀመጠችውን ዕቅድ በሚመለከት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

ከ2013 እስከ 2022 ዓ.ም የሚከናወን የአስር ዓመት “የፍኖተ ብልጽግና” የልማት እቅድ ተዘጋጅቷል።

የፕላን ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ ቀደም ሲል የተከናወኑ የልማት አፈፃፀሞችን፣ አሁናዊ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያና ቀጣይ የሚከናወኑ የልማት እቅዶችን አስፈላጊነትና ዓላማ በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በገለጻቸውም ከ2013 ዓ.ም በፊት በነበሩት አስር አመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ 9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን አመላክተዋል።

በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ፣ በኮንስትራክሽንና በአገልግሎት ዘርፍ የተመዘገበውን ስኬት፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የቀጣይ ዕቅድ ለውይይት መነሻነት አቅርበዋል።

ከ2013 ዓ.ም በፊትም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ዘርፎች ላይ የተሻለ አፈፃጸም ማስመዝገብ ተችሎ እንደነበር አስታውሰዋል።

ነገር ግን ዘገምተኛ ምርታማነት፣ አዝጋሚ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ እድገት፣ የዕዳ ጫና፣ የዋጋ ግሽበት፣ ዝቅተኛ የውጭ ንግድ አፈፃጸም፣ የህግና ተያያዥ የፖሊሲ ተግዳሮቶች ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ዕድገት እንዳታስመዘግብ እንቅፋት ፈጥረውባት እንደነበር አመላክተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን፣ የመዋቅር ክፍተቶችና የክፍላተ-ኢኮኖሚ አዝጋሚነትን ለማስተካከልም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን አንስተዋል።

አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በዕዳ ጫና ቅነሳ፣ በግብርና ምርታማነት በህግና የፖሊሲ ማሻሻያ ላይ ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን ጠቁመዋል።

የአስር ዓመቱን “ፍኖተ ብልጽግና” የልማት ዕቅድ ለማሳካት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስፈፃሚውን አካል በመቆጣጠርና በመገምገም የሚኖራቸው ሚና የጎላ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ የክትትል ስራ ተጠናክሮ የአስፈፃሚው አካል ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ከተደረገ የልማት እቅዱ እንደሚሳካም ተናግረዋል።

የአስር ዓመቱ “ፍኖተ ብልጽግና” የልማት ዕቅድ “ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት” የሚያደርግ መሆኑም ተገልጿል።

የምክር ቤት አባላትም የህዝብን አደራ ለመወጣት፤ የኢትዮጵያ የልማት እቅድ እንዲሳካ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የምክር ቤቱ አባላት አገራዊ የልማት እቅዱን በሚመለከት ላነሷቸው ጥያቄዎች ሚኒስትር ምላሽና ማብራሪ ሰጥተዋል፡፡

በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው 10 በመቶ እድገት በማስመዝገብ “ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት” ለማድረግ ራዕይ መቀመጡ ይታወቃል።