የሸኔ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

መስከረም 27/2014 (ዋልታ) – በምስራቅ ጉጂ ዞን በንፁሃን ዜጎቸ ላይ ጥቃት ለመፈፀም በህቡዕ  ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የሸኔ ታጣቂዎች ላይ  እርምጃ መወሰዱን ለመረጃው ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን አረጋገጡ።

ከሽብርተኛው ህወሓት ጋር ጥምረት በመፍጠር በኦሮሚያ ክልል አንድ አንድ አካባቢዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ለመፈፀም በህቡእ እየተንቀሳቀሰ ያለው ሽብርተኛው የሸኔ ቡድን፣ ሰሞኑን በምስራቅ ጉጂ ዞን በጎሮ ዶላ ወርዳ አዳዲ ቀበሌ እና ልዩ ቦታው ሙጋዮ በተባሉ አካባቢዎች የጥቃት ሙከራ ለማድረግ ታጣቂዎቹን አስርጎ ለማስገባት መሞከሩ ተገልጿል።

ሆኖም የቡድኑን እንቅስቃሴ በሚስጥር ሲከታተሉ በነበሩ የመንግስት ፀጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ ሴራው መክሸፉንና የጥፋት ተልዕኮ  ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቡድኑ አባላትም መደምሰሳቸውን ለመረጃው ቅርበት ያላቸው ምንጮች አረጋግጠዋል።

የቡድኑን የሽብር ጥቃት ከማክሸፍ በተጨማሪም የፀጥታ አካላት በአሸባሪው የሸኔ ቡድን ላይ በወሰዱት እርምጃ በርካታ የቡድኑ ታጣቂዎች ሙትና ቁስለኛ ሲሆኑ፣ በርካቶች መማረካቸውም ተጠቁሟል፡፡

ቡድኑ እየተወሰደበት ያለውን እርምጃ ተከትሎ ሟቾቹ እንዳይታወቁበት እሬሳ ይዞ ሲሸሽ እንደነበር የጠቁሙት ምንጮቻችን፣ በቡድኑ አባላት ላይ በተወሰደው እርምጃ ከቆሰሉት መካከልም ታጣቂ ሀይሉን ሲመሩ ነበሩ የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች እንደሚገኙበት አረጋግጠዋል።

ሽብርተኛውን የሸኔን ቡድን እግር በእግር በመከታተል ሴራውን የማክሸፍና የመደምሰሱ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠሉንም ምንጮቻችን  ከስፍራው አረጋግጠዋል።