የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ማሳሰቢያ ሰጠ

መስከረም 28/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የሳይበር ጥቃት አስመልክቶ ለተቋማት ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡
ኤጀንሲው ባወጣው የማሳሰቢያ መግለጫ ኢትዮጵያ አሁን እያከናወነች ካለችው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ጋር እንዲሁም ሌሎች ቀጣናዊና አለምአቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያና የህዝቦቿ ጠላቶች እና ተባባሪዎቻቸው ከውስጥና ከውጭ ሆነው የሳይበር ምህዳሩን በመጠቀም በተለያዩ የመሰረተ-ልማትና የመረጃ አውታሮች ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ለመፈጸም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም ሊሳካላቸው አልቻለም ብሏል፡፡
ነገር ግን አሁን እየታዩ ያሉት አዝማሚያዎችና ሙከራዎቻቸውን ማሳሰብና ማሳውቅ አስፈልጓል ሲል በመግለጫው አመላክቷል፡፡
እነዚህ እኩይ ዓላማ ያላቸው አካላት በሀገር ውስጥ ሆነው የመሰረተ-ልማትና የመረጃ አውታሮችን እንዲሁም ሲስተሞችን እንዲያስተዳድሩ በተቋማት መብት የተሰጣቸውን (System Admins) ሲሆኑ፣ ነገር ግን ለሙያቸው፣ ለተቋማቸውና ለሀገራቸው ታማኝ ያልሆኑ ጥቂት ጡት ነካሽ ባንዳዎችን በመጠቀም እክል ለመፍጠር እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡
ስለሆነም ማንኛውንም የመሰረተ-ልማትና የመረጃ አውታሮችን እንዲሁም ሲስተሞችን የምታስተዳደሩ መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆናችሁ ተቋማት ሲስተሞችን እንዲያስተዳደሩ መብት የተሰጣቸውን ወይም የተቋማትን የሶሻል ሚዲያ አካውንቶችን እንዲያስተዳድሩ የይለፍ-ቃል እንዲይዙ የተፈቀደላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች (System or Netwok Admins) ትክክለኛውን የሙያ ብቃት እና ጥብቅ የሥነ-ምግባር ማጣራት የተደረገባቸው መሆኑን ደግማችሁ፣ ደጋግማችሁ እንድታረጋግጡ እናሳስባለን ብሏል ኤጀንሲ በመግለጫው፡፡