በዛሪማ ከተማ ለሰራዊቱ ደጀን የሆኑ ነዋሪዎች በቀጣይ ግዳጅ ከመከላከያ ጎን በመሰለፍ ትግላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ

አንጓች ሰረጠ

መስከረም 29/2014 (ዋልታ) በማይጠብሪ ግንባር ዛሪማ ከተማ ለሰራዊቱ ደጀን የሆኑ ነዋሪዎች በቀጣይ ግዳጅ ከመከላከያ ጎን በመሰለፍ ትግላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ፡፡

ወራሪውና አሸባሪው ሕወሓት ሽንፈት በደረሰበት የዛሪማ አውደ ውጊያ የአካባቢው ማህበረሰብ የቆሰሉ የወገን ወታደሮችን ከጠላት ሸሽገው በማትረፍ ትልቅ ጀብድ ፈፅመዋል፡፡

በሰሜን ጎንደር የዛሪማ ከተማ ነዋሪዎች የሆኑት አንጓች ሰረጠ እና ካሳ ጥላሁን እንደገለጹት ንብረታቸው በወራሪው ትህነግ ተዘርፎባቸዋል፡፡

በማይጠብሪ ግንባር ነሐሴ ላይ በነበረው ከባድ ጦርነት የቆሰሉ አራት የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ከጠላት ሸሽገው ከወር ላለነሰ ጊዜ አክመውና ተንከባክበው ህይወታቸውን እንዳተረፉም ለዋልታ ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በነበረው ከባድ ውጊያ ወራሪው ቡድን ከአካባቢው ከመውጣቱ በፊት ቆስለው ወደ ማህበረሰቡ የተጠለሉ የሰራዊቱ አባላት ከባድ አደጋ ተጋርጦባቸው እንደነበር የሚያስታወሱት ነዋሪዎቹ፣ ወታደሮቹን ደብቀው እያከሙ የነበሩ ነዋሪዎች ህይወታቸውም ስጋት ላይ ወድቆ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ካሳ ጥላሁን

የጁንታው አባላትም በጥርጣሬ ይመረምሩና ይከታተሉ እንደነበር የወታደሮቹ ደጀን የሆኑት አቶ ካሳ እና ወይዘሪት አንጓችን አስታውሰዋል፡፡ በጦርነቱ የቆሰሉት የሰራዊቱ አባላትም በጠላት እጅ እንዳይገቡባቸው እስከ ህይወት መስዋእትነት ለመክፈል ቁርጠኛ እንደነበሩም ወገንተኝታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሆነው ሆኖ የሀገር መከላከያ ወራሪውን ቡድን በገባበት ካሰቀረና ቦታዎችንም ነፃ ካወጣ በኃላ የአባቢው ነዋሪ ተንከባክበው ያቆዩዋቸውን ቁስለኛ ወታደሮች በክብር አስረክበዋል፡፡

የዛሪማ ነዋሪዎችም በዚህ ረገድ የሰሩት ተጋድሎ ለታሪክ ተቀምጧል፡፡ ከትህነግ ነፃ ያልወጡ ቦታዎችን ለማስለቀቅና የተጀመረውን የህልውና ዘመቻም በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ከመከላከያ ጎን ተሰልፎ ትግሉን እንደሚያጠናክር ጠይቀዋል፡፡ የአካባቢው ወጣቱም ሰለጥኖና ታጥቆ የጠላትን ኃይል ለመደምሰስ በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በደምሰው በነበሩ (ከማይጠብሪ ግንባር)