የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባቸው የቦኖ ውሃዎች አስመረቀ

መስከረም 30/2014 (ዋልታ) የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በገንደ ተስፋ ለገ-ኦዳ አንድ ሺሕ 800 የአካባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ከ450 ሺሕ ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸውን ሶስት የቦኖ ውሃዎችን ከፍተኛ የአስተዳደሩ አመራሮች በተገኙበት አስመረቀ።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ኡባህ አደም (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው ሶስት የውሃ ቦኖዎችን 450 ሺሕ ብር በሆነ ወጪ ማስገንባቱን ጠቅሰው በቀጣይም ነዋሪውን በሰፊው በማወያየት የሚነሱ ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ዩኒቨርሲቲው እንደሚሰራም ገልጸዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የሰው ልጅ በህይወት ለመኖር ውሀ በእጅጉ እንደሚያስፈልገው ገልፀው፣ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ላሰራቸው የውሀ ቦኖዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በማህበረሰብ ስራዎች ላይም አስተዳደሩ እገዛውን በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው ከፍተኛ የውሀ ችግር እንደነበር ተናግረው፣ አሁን ላይ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢያቸው የውሀ ቦኖ በማሰራቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
በፕሮግራሙ ላይም ከፍተኛ የአስተዳደሩና የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የገንደ ተስፋ ለገ-ኦዳ አካባቢው ነዋሪዎች መሳተፋቸውን ከድሬዳዋ ኮዩሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።