2,756 ጥይት እና 51 ሽጉጥ በመኖሪያ ቤታቸው የደበቁ ግለሰቦች ተያዙ

ጥቅምት 02/2014 (ዋልታ) በባህርዳር ከተማ አስተዳደር በሁለት ግለሰቦች መኖሪያ ቤት በተደረገ ፍተሻ 2 ሺህ 756 የተለያየ ዓይነት ጥይትና 51 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ከሁለት ተጠርጣሪ ግለሰቦች ጋር መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።

በከተማው የ9ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ኮማንደር ንብረቱ ሞላ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያው የተያዘው ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት ፖሊስ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት በጋራ በተደረገ ክትትል ዛሬ ከሰዓት በፊት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ነው።

በከተማው ዳግማዊ ምኒሊክ ክፍለ ከተማ ውስጥ ማርዘነብ ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ በተደረገው ድንገተኛ ፍተሻ 2 ሺህ 177 የብሬን፣ 222 የሽጉጥና 69 የክላሽንኮቭ ጥይት እንዲሁም 50 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ከነተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልፀዋል።

የጦር መሳሪያዎቹን ከጎንደር እንዳመጣቸው በግለሰቡ ላይ በተደረገ ምርመራ መረጋገጡን ጠቅሰው፤ ግለሰቡ ሙሉ ግቢ ቤት ተከራይቶ ህገ ወጥ ስራውን ይስራ እንደነበረም አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ ዛሬ ከሰዓት ቀበሌ 09 በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ በአንድ ግለሰብ ቤት ውስጥ 288 የክላሽንኮቭ ጥይት ከነ ተጠርጣሪ ግለሰቡ መያዙንም ሃላፊው ጨምረው አስታውቀዋል።

በወንጀሉ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ሁለቱም ግለሰቦች በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ኮማንደሩ አስታውቀዋል።