ኢትዮጵያን ከ”አጉዋ” የንግድ ስርዓት ለማስወጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ጥቅምት 02/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያን ከ”አጉዋ” የንግድ ስርዓት ለማስወጣት እየተደረገ ያለው ጥረት ተገቢነት የጎደለው እንደሆነ ተገለጸ፡፡

አሜሪካ ከሰሃራ በታች ያሉ አገራትን ኢኮኖሚ ለመደገፍ የቀረፀችው ምርቶችን ከቀረጥ ነፃ ወደ አገሪቱ የማስገባት የንግድ ዕድል “አግዋ” ይሰኛል፡፡

በዚህ ዕድል ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ታዳጊ የአፍሪካ አገራት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአሸባሪው ህወሓት ሎቢስቶችና ፀረ ኢትዮጵያ አቋም የሚያራምዱ ሌሎች አካላት ከዚህ ወሳኝ የንግድ ስርዓት ኢትዮጵያ እንድትሰረዝ ጥረት እያደረጉ ይገኛል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሳንዱካን ደበበ ይህ እኩይ ተግባር በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ተቀጥሮ የሚሰራውን ዝቅተኛውን የማህበረሰብ ክፍል የሚጎዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ ከሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች 41 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኘው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ35 ሺሕ በላይ ዜጎች ተቀጥረው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

በፓርኩ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርት ላይ የተሰማሩ 23 ኩባንያዎች ይገኛሉ፡፡

እነዚህ ኩባንያዎች ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን ምርታቸውን ለአሜሪካ ገበያ የሚያቀርቡ ሲሆን፣ አሁን ኢትዮጵያን ከ”አግዋ” ለማስወጣት የሚደረገው ጥረት ይህን ገበያ ለማሳጣት ያለመ ነው፡፡

ዋልታ ያነጋገራቸው በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙ ሰራተኞች አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአግዋ የምታስወጣ ከሆነ ስራቸውና ህይወታቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ዓመት ብቻ በኢንዱስትሪ ፓርኮቿ ካመረተቻቸው ምርቶች 240 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ያገኘች ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 144 ሚሊዮን ዶላሩ በሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ የተገኘ ነው፡፡

በሳሙኤል ሀጎስ