የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነትን መቀበል ብቻ ሳይሆን ሰርተው ውጤት ማምጣት እንደሚጠበቅባቸው አቶ ሉምባ ደምሴ ገለጹ

በአዲሱ የመንግሥት ምስረታ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተካተቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነትን መቀበል ብቻ ሳይሆን ሰርተው ውጤት ማምጣት እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) የድርጅት ጉዳይና የጽህፈት ቤት ኃላፊ ሉምባ ደምሴ ገለጹ።
በደቡብ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ ሉምባ እንደገለጹት፣ አዲስ በተመሰረተው መንግሥት ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካተታቸው ትልቅ እድል ነው።
አብሮ መሥራት ኃላፊነት መጋራት ብቻ አይደለምያሉት ኃላፊው፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ ስንሰራ ሕዝቡ ውስጥ አንድነትና ሰላም ይሰፍናል፤ ለአገራችንም ገጽታ መልካም ነው ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
ከለውጡ በፊት እንወያይ የሚል ጥያቄ በመያዝ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ድረስ ደብዳቤ በመያዝ ሄደው እንደነበረ ያስታወሱት የቢሮ ኃላፊው፣ በውይይት ተቀራርቦ ለጋራ አገር አብሮ ከመስራት ይልቅ መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ ብቻ እንደ ማስታገሻ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ይጠቀም ነበር ብለዋል።