ለሀገር ብልፅግና የሚሰሩ ወጣቶችን ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ

ጥቅምት 5/2014 (ዋልታ) ለህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ለሀገር ብልፅግና የሚሰሩ ወጣቶችን ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተክለ በዛብህ ገለጹ፡፡

በዳውሮ ዞን በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ አገልግሎት የመዝጊያና የ2014 ዓ.ም የበጋ ወራት የወጣቶች በጎ አገልግሎት የማስጀመሪያ መርኃግብር ተካሂዷል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው በዞኑ ውስጥ በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት በተለያዩ የበጎ ተግባራት ተሰማርተው ማህበረሰቡን ያገለገሉ ወጣቶችን አመስግነዋል፡፡

ወጣቶች በ2014 ዓ.ም የበጋ ወራት የበጎ አገልግሎት በክረምት የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ተግባር ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በዳውሮ ዞን በ2013 በጀት ዓመት የክረምት ወራት ከ52 ሺሕ በላይ በጎ ወጣቶች በ10 የተለያዩ የበጎ ተግባራት በመሰማራት ከ300 ሺሕ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን የዞኑ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ውብአለም በዛብህ መናገራቸውን ከዞኑ ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በበጎ ፈቃድ አገለግሎት ለሀገር ብልፅግናና ለማህበረሰብ ተጠቃሚነት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆኑንም ተመላክቷል።