ተመድ በኬንያዊቷ ሰራተኛ ላይ የወሰደው እርምጃ የድርጅቱን ትክክለኛ መልክ ያሳየ መሆኑ ተገለጸ

የተባበሩት መንግስታት ሥነ ህዝብ ጽህፈት ቤት የኢትዮጵያ ኃላፊ የሆነችው የኬንያዊቷ ሰራተኛ ከስራ መታገድ የድርጅቱን ትክክለኛ መልክ ያሳየ መሆኑን በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ንጉሴ በላይ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኬንያዊቷ ሰራተኛ የተባበሩት መንግስታት በኢትዮጵያ ላይ ትክክለኛ አቋም እንዳልያዘና የሕወሓትን የሽብር ቡድን እያገዘው እንደሆነ የሚገልጽ መረጃ አሳልፋ በመስጠቷ ከስራ መታገዷ የድርጅቱን ትክክለኛ መልክ አሳይቷል ብለዋል።
እንደ ባለሙያው ንግግር ዴኒያ ጌይል የተባለችው ሰራተኛ የተባበሩት መንግስታት እየተከተለ ያለው አካሄድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፋና ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ የሚያደርግ መሆኑንና የውጭ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ እያሳረፉት ያሉት ተፅዕኖ አንዱ አካል ነው ብላ በመናገሯ ከስራ እንድትታገድ አድርጓታል፡፡
“የተባበሩት መንግስታት በአፍሪካና በሌሎች የኢስያ ሀገራት ላይ በሰብዓዊ ዕርዳታ ስም የምዕራባውያንን ተልዕኮ ለማስፈጸም የሚሄዱበትን ርቀት ኢትዮጵያ ላይ ከሚያደርጉት ነገር በመነሳት መረዳት ይቻላል” ያሉት ንጉሴ (ዶ/ር)፣ በዚህም ድርጅቱ ለደሃ ሀገራት ያለውን ትክክለኛ አቋም ከኬንያዊቷ ሰራተኛ ለማወቅ ተችሏል ብለዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።