በቤንች ሸኮ ዞን የፕሮጀክቶች ጉብኝት ተደረገ

ጥቅምት 10/2014 (ዋልታ) የቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ አመራሮች በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር በመገንባት ላይ የሚገኙ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ፡፡

በዞኑ አስተዳደር በመገንባት ላይ ያለው የባህል ማዕከል ጉብኝት ከተደረገባቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሲሆን ለግንባታው ከ344 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ተገልጿል።

ግንባታው ካጋጠመው የንድፍ (ዲዛይን) ለውጥ ውጭ የከፋ ችግር እንዳላጋጠመ የተናገሩት የፕሮጀክቱ ኃላፊ በረከትአብ ጨመረ ግንባታውን በ3 ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ሌላው ፕሮጀክት በ67 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ወጪ በመገንባት ላይ ያለው የሚዛን አማን ሁለገብ ስታዲየም ነው።

የስታዲየሙ ግንባታ የተጀመረው በሳለፍነው ሐምሌ ሲሆን በሦስት ወር ውስጥ ፈጣን ለውጥ እያሳየ መሆኑን የፕሮጀክቱ ኃላፊ ባህሩ ኸይረዲን ተናግረዋል። ከተያዘለት ጊዜ አንድ ዓመት ቀድሞ ይጠናቀቃልም ነው የተባለው።

በተጨማሪም በዞኑ አስተዳደር በመገንባት ላይ ያሉት የአካል ጉዳተኞች ተሀድሶ ማዕከል፣ የስፖርት ማዕከል፣ የቤንች ሸኮ ሁለገብ አዳራሽ እና የተለያዩ በከተማዋ ባላሃብቶች በመገንባት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ተጎብኘተዋል፡፡

በሔለን ታደሰ