የሳይበር ደህንነትን የማስጠበቅ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ጥቅምት 12/2014 (ዋልታ) የሳይበር ደህንነትን የማስጠበቅ ስራን አስመልክቶ ለክልል እና ከተማ አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች እና ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሠጠ ይገኛል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ የሳይበር ደህንነት ወር ከጥቅምት 1 ጀምሮ እየተከበረ ነው፡፡

“ወሩ የሳይበር ደህንነት የጋራ ኃላፊነት ነው እንወቅ እንጠንቀቅ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ሲሆን፣ ሥልጠናውም ሠልጣኞቹ ስለሳይበር ደህንነት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ታስቦ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አንተነህ ተስፋዬ (ዶ/ር) ሳይበር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰው ልጅ ላይ አዎንታዊ እና አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ በመሆኑ ተቋሙ ለዜጎች የሳይበርን ምንነት እና ደህንነትን የማሳወቅ ስራ ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።

የሳይበር ጥቃት ከሚያስከትለው  የፋይናንስ ክስረት በተጨማሪ ሀገራዊ ሉአላዊነትን ማሳጣትን ጨምሮ ዲፕሎማሳዊ ጉዳቶችንም የሚያስከትል በመሆኑ ለኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች እና ለፖሊስ ኮሚሽነሮች በቂ ግንዛቤን በመፍጠር የሳይበር ጥቃትን አስቀድሞ ለመከላከል ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

ከስልጠናው ጎን ለጎን ሠልጣኞቹ የኤጄንሲውን ምርት እና አገልግሎቶችን ይጎበኛሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በሳይበር ጥቃት ምክንያት በአለም 2 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር ማጣቷን መረጃዎች ይጠቁሟሉ።

በድልአብ ለማ