የትምህርት አሰጣጥ ሂደትን  ለማዘመን መንግስት ትኩረት ይሰጣል –  ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) 

ጥቅምት 18/2014 (ዋልታ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እና የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱን ለማዘመን መንግስት ትኩረት እንደሚሰጥ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ከተወጣጡ አመራሮች ጋር ውይይት እያካሄዱ ነው።
ተቋማቱ የአስተዳደር እና የመሰረተ ልማት ችግሮች እንደሚስተዋልባቸው ያነሱት ሚኒስትሩ የላብራቶሪ እና የአይቲ መሰረት ልማት አለመሟላትም ከሚገጥሟቸው ፈተናዎች ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል።
ሚኒስትሩ አብዛኛዎቹ ዩኒቨርስቲዎች ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ የሚነሳባቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲችሉ ያሉባቸውን ክፍተቶች በአፋጣኝ ለይተው የመፍትሄ እርምጃዎችን እንዲወስዱም መመሪያም ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል ዩኒቨርስቲዎች የፌዴራል ተቋማት እንጂ የክልል ተቋማት አይደሉም ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ህዝብን እንጂ ማንኛውንም የፖለቲካ አቋም አራማጅ መሆን እንደሌለባቸውም አሳስበዋል።
ከመንግስት ተጽዕኖ ነጻ የሆነ አሰራር ለመመስረት እንዲሁም አካባቢያዊነትን፣ ሌብነትንና የሃብት ብክነትን ለማስቀረትም ዩኒቨርስቲዎቹ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ ይገባል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡