የትህነግ ቡድን እስከወዲያኛው ላይመለስ በአጠረ ጊዜ ልንሸኘው ይገባል – ብልፅግና ፓርቲ

ጥቅምት 20/2014 (ዋልታ) – የአሸባሪው ትሕነግ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ከንቱ ምኞትን በሚገባው ቋንቋ አስረድተን እስከወዲያኛው ላይመለስ በአጠረ ጊዜ ልንሸኘው ይገባል ሲል ብልፅግና ፓርቲ ጥሪ አቀረበ፡፡

ፓርቲው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባወጣው ሐተታ አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን በቅጥፈት እጆቹ ጠፍጥፎ የጋገራት ህብስት አድርጎ በመቁጠር እሱ ባሻው ሰዓት የሚያቦካትና የሚፈረካክሳት ጡብ አድርጎ ይቆጥራታል ብሏል።

ነገር ግን ኢትዮጵያዊያንን በጎሳ እና በመንደር በመከፋፈል ኢትዮጵያ ኅልውናዋን መቼም ልታጣ አትችልም ሲል በአጽንኦት ገልጿል።

ኢትዮጵያዊነት የኅብር መገለጫ የዜግነት ክብር እና ኢትዮጵያዊ በመሆን ብቻ የሚገነዘቡት እውነት እንጂ አየር ላይ የተበተነ ጉም አይደለም ሲልም ነው ያብራራው፡፡

አያይዞም ሽብርተኛው የትሕነግ ቡድን በአገሪቱ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ መከራ ሲዘራና ሲያሳጭድ መቆየቱን የጠቀሰው ብልጽግና ፓርቲ ነፃ አወጣዋለሁ የሚለውንም የትግራይ ሕዝብ በነፃ አውጪ ስም በርካታ ግፍና መከራ ሲያሸክመው መኖሩን አስረድቷል።

አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ከወራሪ ጠላት ጠብቀው ያስረከቡንን ውድ አገራችንን የወቅቱ የጋራ ጠላታችን የሆነው ትሕነግ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ከንቱ ምኞቱን በሚገባው ቋንቋ አስረድተን እስከወዲያኛው ላይመለስ በአጠረ ጊዜ ልንሸኘው ይገባል ብሏል ፓርቲው፡፡

ኢትዮጵያዊነትን በማንኳሰስ የሚለወጥ አንዳች ነገር እንደሌለ የገለጸው ብልጽግና ፓርቲ አገር የሁላችንም ምሰሶ ናት አገር ከግለሰቦችና ከቡድኖች በላይ ናት፤ እንደ አፈ ቀላጤዎቹ ቢሆንማ ኖሮ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ልትኖር አትችልም ነበር ብሏል።