በጊቤ አንድ ኃይል ማመንጫ ግድብ ውኃው ሳይፈስ ስኬታማ ጥገና ተከናወነ

ጥቅምት 22/2014 (ዋልታ) በጊቤ አንድ ኃይል ማመንጫ ግድብ ውኃው ሳይፈስ ከ18 ሜትር ጥልቀት በላይ ወደ ውኃ ውስጥ በመግባት ስኬታማ ጥገና መከናወኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ደሳለኝ ንጉሳ ገለጹ፡፡

ግድቡ ላይ 1 ነጥብ 5 ሜትር ክበት ስንጥቅ በመኖሩ ግድቡ ውኃ የማስረግ ችግር ገጥሞት እንደነበር የገለፁት ሥራ አስኪያጁ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ውኃው ሳይፈስ ጥገናውን በማከናወን ችግሩን መቅረፍ ተችሏል ብለዋል፡፡

የቻይናው ሲ ጂ ጂ ሲ ኩባንያ የጥገና ሥራውን ያከናወነ ሲሆን ውኃው ሳይፈስ በመጠገን ለኃይል ማመንጫው በቂ የውሃ ክምችት እንዲኖር አስችሏልም ነው የተባለው፡፡

የደለል ማስወገጃና መቆጣጠሪያ አሸንዳ በጉዳት ምክንያት አገልግሎት መስጠት አቋርጦ የነበረ መሆኑን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፣ ጥገና ተከናውኖለት ወደ ሥራ ለማስገባት የሙከራ እና የፍተሻ ሥራዎች መከናወናቸውንም መግለፃቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለጥገናው አጋዥ የሆኑ የመቆጣጠሪያ ሰሌዳ እና የሞተር ፓምፕ ገጠማ ሥራዎችም ተከናውኗል ተብሏል፡፡

በ1996 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጊቤ አንድ የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 184 ሜጋ ዋት ኢነርጂ የማመንጨት አቅም አለው፡፡