የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥሪ ለወጣቶች

ጥቅምት 22/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች የመከላከያ ኃይልን በመቀላቀል የህልውና አደጋውን ለመቀልበስ ከመቼውም በላቀ ቁርጠኝነት ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማት እና የውጊያ ግንባሮች እንዲተሙ ጠየቀ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጠየቀ።
አስተዳደሩ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሰጠው ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦
የህወሓት ከሃዲ ጁንታ ሥልጣኔን አሳጥተውኛል ብሎ በሚያስባቸው ወገኖችና መላ ኢትዮጵያውያን ላይ ጠንካራ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ይፋዊ ጦርነት ከከፈተብን አንድ ዓመት ሞላው።
ከሃዲው የትህነግ ጁንታ የዛሬ ዓመት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ከ20 ዓመታት በላይ በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ ሲጠብቀው በኖረው የሰሜን እዝ የመከላከያ ኃይላችን ላይ ታሪክ የማይረሳው ክህደት ከፈጸመ በኋላ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ሁሉንም አይነት ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል።
የትህነግ አሸባሪ ቡድን በአሁኑ ወቅት ያለሃፍረት “ኢትዮጵያ ሳትፈርስ ነጻ ሃገረ ትግራይን መመስረት አይቻልም” የሚል ግልጽ ዓላማ አንግቦ እየተፋለመን ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያግዙትን የውስጥ እና የውጪ አሸባሪዎች እና ታሪካዊ ጠላቶቻችንን አስተባብሮ በሁሉም አቅጣጫ ውጊያ ከፍቶብናል።
አሸባሪው ኃይል በክልሉና ከክልሉ ውጪ የሚኖረውን የትግራይ ሕዝብ በዘረኝነት እና በሀሰት ፕሮፓጋንዳ በማስከርም በወረራ በተቆጣጠራቸው የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች አስከፊ ግድያ እና ዝርፊያ እየፈጸመ ነው።
በዚህ ምክንያት በኛ ዘመን እጅግ የምንወዳትና እንደ አይናችን ብሌን የምንሳሳላት ሃገራችን የተባበረ ጥቃት ሰለባ ሆናለች።
እናም ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን በመቆም ሃገራችንን መታደግ የግድ ከሚለን የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ነን። እንደ ሃገርም ቁርጠኛና የተናበበ አመራር ከምንሰጥበትና የተደራጀ የሕዝብ ንቅናቄ ከምናረጋግጥበት የትግል ምዕራፍ ውስጥ እንገኛለን።
ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል የገጠሙኣትን የህልውና አደጋዎች በሙሉ የቀለበሰችው በሕዝቦቹኣ ጠንካራ አንድነትና የተባበረ ክንድ ነው።
በዚህ ዘመን ኢትዮጵያን ካልዘረፍኳትና እንደወትሮው ረግጬ ካልገዛኋት ትፍረስ በሚል ስግብግብ ፍላጎት ክህደት የፈጸመብንና ጦርነት የከፈተብንን የህወሓትን ወራሪ ጁንታ የምንሰብረውና የምንቀብረውም ከታሪካችን በወረስነው በዚሁ የጀግንነትና የአንድነት መንፈስ ብቻ ነው።
በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሸባሪው የህወሓት ጁንታ የከፈተብን ሁለገብ ጥቃት የደረሰበትን ደረጃ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሁለንተናዊ አቅሙን ሃገራችን የተጋረጠባትን አደጋ ለመቀልበስ በሚያስችሉ እርምጃዎች ላይ ለማዋል ወስኗል።
የአዲስ አበባ አበባ ከተማ አስተዳደር የህወሓት ዘራፊ ጁንታ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ቀጥተኛ ወረራ ከፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ አመራሩን፣ ባለሃብቱንና መላ የከተማውን ነዋሪዎች በማስተባበር ለመከላከያ ኃይላችንና በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል 4 ቢሊዮን ብር ያህል ሃብት በማሰባሰብ ለፌደራል እና ለክልል መንግስታት አስረክቡኣል።
የከተማ አስተዳደራችን ዛሬም በየግንባሩ በጽናትና በጀግንነት የሚፋለሙት የመከላከያ ሰራዊታችንና መላ የፀጥታ ኃይሎቻችን ጠንካራ ደጀን ከመሆን ባሻገር አመራሩንና ሕዝቡን በማስተባበር በግንባር በመሰለፍ ሁሉንም አይነት መስዋዕትነት አብሮአቸው ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል።
የከተማ አስተዳደሩ በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ በአጭር ጊዜ ለመቀልበስ ከሕዝቡና ከሁሉም የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በቁጭትና በጥድፊያ መንፈስ እንደሚሰራም በዚሁ አጋጣሚ ይገልጻል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስትና ዓራት ዓመታት የታየውን ሁለንተናዊ ለውጥ የፈጠሩት በባዶ እጃቸው አደባባይ ወጥተው የህወሓትን የአፈና ታንኮች የገጠሙ ፍትህና ዕኩልነት የጠማቸው ወጣቶችና ጭቆና የበረታባቸው ዜጎች ናቸው።
የህወሓት አሸባሪ ኃይል ዛሬ በየአንዳንዳችን ደጀፍ ለመድረስ እየማሰነ ያለው ይህንኑ ነባራዊ ዕውነት ለመመለስ ነው።
በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች በመቶ ሺዎች ተደራጅተው የአካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ ከመጠበቅ በተጨማሪ በገፍ የመከላከያ ኃይላችንን በመቀላቀል የህልውና አደጋውን ለመቀልበስ ከመቼውም በላቀ ቁርጠኝነት ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማትና የውጊያ ግንባሮች እንዲተሙም አስተዳደራችን ጥሪውን ያስተላልፋል።
የከተማው ነዋሪዎችም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በመኖሪያ አካባቢዎች ደረጃ በመደራጀት እና ከሁሉም የፀጥታና የአስተዳደሩ አካላት ጋር በመናበብ ሰላምና ፀጥታቸውን በንቃትና በብቃት እንዲጠብቁ ይጠይቃል።
የከተማው የመኖሪያ ቤት አከራዮች፣ ሆቴሎችና ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቃማት አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ሰርጎ ገቦችን ለመቀጣጠር የሚፈጸሙ መደበኛና ድንገተኛ ፍተሻዎችን ከመደገፍ በተጨማሪ ተገልጋዮቻቸውን በቅርበት እንዲከታተሉም የከተማ አስተዳደሩ ያሳስባል።
የከተማ አስተዳደሩ በዚህ አጋጣሚ በህወሓት አስተባባሪነት በግንባር የሚፈጸመውን የሽብር ድርጊት በከተማችን ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚደግፉ ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴዎች ላይ ቋሚ ፣ ህጋዊና ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ ያሳውቃል።
የከተማችን ነዋሪዎችና መላው ኢትዮጵያውያን በዚህ ወሳኝ ወቅት አንድ ሆነው በመቆማና ሁለገብ አቅማችሁን በማስተባበር የሽብር ቡድኑን ይልፈት ለማፋጠን የሚያስችል ፈጣንና ወሳኝ እርምጃ እንድትዎስዱ የከተማ አስተዳደራችሁ ጥሪውን ያስተላልፍላችኋል።