11ኛው ክልል የህዝቦችን ጥያቄና ፍላጎት መሰረት ያደረገ ነው – የዳውሮ ዞን አስተዳደር

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተክሌ በዛብህ

ጥቅምት 23/2014 (ዋልታ) አዲሱ 11ኛ ክልል ሆኖ የሚመሰረተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አደረጃጀት የህዝቦችን ጥያቄና ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆኑን የዳውሮ ዞን አስተዳደር ገለጸ፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ተክሌ በዛብህ ከዋልታ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ህዝቡ የራሱን ክልል ለመመስረት ዴሞክራሲያዊ መብቱን ህገመንግስቱ በሚያዘው መሰረት በህዝበ ውሳኔ ድምጹን የሰጠበትና በዚህም ምላሽ ያገኘበት ነው፡፡

የዳውሮ ዞን ህዝብ በራሱ ክልል ለመደራጀት በዞን ምክር ቤት በመወሰን ጥያቄ ማቅረቡን ያስታወሱት አስተዳዳሪው መንግስት ባመጣው አማራጭ ሃሳብ ዳግም ውሳኔውን በማሻሻል የዳውሮ ዞን ከአራት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ ጋር እንደ አንድ ክልል ለመደራጀት መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ብሔረሰቦች ተመሳሳይ ሥነ ልቦና እና አብሮ የመልማት ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው ከዚህ በፊት በነበረው አደረጃጀት ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዳልነበረና ህዝቡ ከተለያዩ መሠረተልማቶች ተገለው እንደቆዩ ጠቁመዋል፡፡ አሁን ላይ ግን አዲሱ ክልል አካባቢው ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲለማ ዕድል እንደሚሰጥ አመልክተዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በመጣው የለውጥ መንግስት የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እያገኘ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በአዲሱ የክልል አደረጃጀት በከተሞች ሥርጭት ትኩረት ተደርጎ በክላስተር ደረጃ ከተሞችን የማደራጀት ሥራ እንደሚሰራ ያመለከቱት አስተዳዳሪው የክልል ቢሮዎች የማይኖርባቸው አካባቢዎችን በእኩል ለማልማት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የክልሉን አደረጃጀት በተመለከተ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ህዝቡ እየተወያየበት መሆኑን ገልጸው፣ ይህም በየአካባቢው ያሉ የተለያዩ አንጡራ ሃብቶች መጠቀምን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በአድማሱ አራጋው