እንደ ሃገር የመጣብንን አደጋ አንድ ሆነን እንመክተዋለን – የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ

የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ

ጥቅምት 23/2014 (ዋልታ) እንደ ሃገር የመጣብንን አደጋ አንድ ሆነን እንመክተዋለን ሲል የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ገለፀ፡፡

ይህ ጠላት በአፋርና በአማራ ክልሎች ላይ ወረራ ይፈፅም እንጂ በከፍተኛ የበቀልና የጥላቻ ስሜት የመጣ  የመላው ኢትዮጵያውያን ጠላት ነው ብሏል ፅህፈት ቤቱ፡፡

ይህን ጥላቻውን ለሶስት አስርት አመታት በስልጣን በነበረበት ጊዜ ሁሉንም  ጠላት አድርጎ ሲያስር፣ ሲገድል፣ ሲያሰቃይ፣ ሲዘርፍና ሲያዋርድ የኖረ፥ ኦሮሞውን በሙሉ ኦነግ እያለ ሲጨፈጭፍ፣ ከሃገር ሲያባርር፣ እስር ቤቱን በኦሮምኛ ተናጋሪ አጭቆ የእስር ቤት ቋንቋ ሲያደርግ፣ መሬቱን ሲቀማና ሃብቱን ሲዘርፍ የኖረ ነው  ሲል ገልጿል፡፡

እንዲሁም አማራውን ጠላት ብሎ ፈርጆ ሁለንተናዊ ጥቃት ሲያደርስበት በሃገሩ መኖር እስከሚያቅተው ከፍተኛ በደል ሲያድርስ የኖረ፣ ሶማሌውን፣ አፋሩን፣ ጋምቤላውን፣ ቤኒሻንጉሉን እና ሃረሪውን በሃገሩ ጉዳይ እንዳይወስን ሁለተኛ ደረጃ ዜግነት የሰጠ ከራሱ ጥቅም ለማንም ውግን እና ርህራሄ የሌለው ጨካኝና አረመኔ ቡድን ነው ብሏል።

ስለሆነም ይህንን ሃይል በብቃት ልንመክትና ሃገራችንን ልንከላከል የምንችለው እንደ ህዝብ ያለ ልዩነት መላው ኢትዮጵያውያን ተደራጅተን በአንድነት ስንቆም ብቻ ነው ብሏል የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት፡፡