“ኢትዮጵያ የገጠማት ጦርነት ከሽብር ቡድኑና ግብረአበሮች ጋር ብቻ የሚካሄድ ግጭት አይደለም” ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ

ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ

ጥቅምት 24/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ጥቅምት 24 ቀን 2013 በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ አሸባሪው ሕወሓት የፈጸመውን ክህደትና ጥቃት አንደኛ ዓመት መታሰቢያን አስመልክቶ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የገጠማት ጦርነት የሰራዊት ለሰራዊት ወይም ከሽብር ቡድኑና ግብረአበሮች ጋር ብቻ የሚካሄድ ግጭት አይደለም።

“ጦርነቱ በሁለት የታጠቁ ኃይሎች መካከል ሳይሆን የውክልና፣ የዘረፋና አንድን ህዝብ በዘር አነሳስቶ በሌሎች ላይ የመዝመት አደገኛ ጦርነት ነው” ብለዋል።

በመሆኑም መላው ህዝብ ለአገሩ ዘብ መቆም እንዳለበት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ አስገንዝበዋል።

እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ጋር ብቻ እንዳልሆነ መታወቅ እንዳለበትም ገልጸዋል።

“ስለዚህም መላው የአገራችን ህዝቦች፣ የክልል ፀጥታ ሀይሎች፣ ሚሊሻዎች፣ ኢትዮዽያን የሚወዱ ወጣቶችና ማንኛውም ዜጋ የመጣውን አደጋ ለመከላከል ተነስ” ሲሉ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ጀኔራል ብርሃኑ አሳስበዋል።

ወቅቱ ህልውና ለማስጠበቅ የምንነሳበት እንጂ እያንዳንዱ ሰው ትችት እየሰነዘረ ትንታኔ እየሰጠ የሚቀጥልበት እንዳልሆነ ግንዛቤ መያዝ እንዳለበትም አመልክተዋል።

“መላው ህዝብ ነቅሎ መነሳት ካልቻለ አገር ይፈርሳል፣ ክልሎች ይዘረፋሉ፣ ከዚህም በላይ ዜጎች ለስደት፣ ለሞትና ለስቃይ እንደሚዳረጉ መታወቅ አለበት” ብለዋል።

ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት ማድረግ ያለበትን ሁሉ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፤ “ጦርነቱ የሁለት የታጠቁ ሃይሎች ሳይሆን የውክልና፣ የዘረፋና አንድን ህዝብ በዘር አነሳስቶ በሌሎች ላይ የመዝመት አደገኛ ጦርነት ነው” ብለዋል።

ግጭቱ የሰራዊት ብቻ ስላልሆነ ከፍተኛ ብሔራዊ አቅምን በማሟጠጥ መጠቀምን የሚጠይቅ መሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።