ከህግ ውጪ ሲሰሩ የተገኙ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

ጥቅምት 25/2014 (ዋልታ) የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በመገንዘብ የንግድ ሥርዓቱን ለማዛባት ሲሰሩ የተገኙ ህገ – ወጥ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ፡፡

የኢፌዴሪ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከወሰደባቸው 23 ሺሕ 300 ያለንግድ ፈቃድ ሲሰሩ የተገኙ፣ 14 ሺሕ 215 ያለደረሰኝ ግብይት የፈፀሙ፣ 2 ሺሕ 466 በምርቶች ላይ ባዕድ ነገር የቀላቀሉ፣ 20 ሺሕ 325 አላግባብ ዋጋ የጨመሩ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም 21 ሺሕ 246 የዋጋ ዝርዝር ያልለጠፉ፣ 3 ሺሕ 100 የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች እንዲሁም 9 ሺሕ 249 ምርት በክምችት ይዘው የተገኙ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡

የንግድ ሥርዓቱን በመጣስ የሀገርን ኢኮኖሚ፣ የህዝቡን የኑሮና ጤና ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ ሲሰሩ በተገኙ 82 ሺሕ 850 ህገ-ወጥ የንግድ ድርጅቶች ላይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው፣ 60 ሺሕ 699 የታሸጉ፣ 1 ሺሕ 242 የታገዱ፣ 924 ንግድ ፈቃድ ስረዛ የተደረገባቸው ሲሆኑ 519 የንግድ ድርጅቶች ተከሰው ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የንግድ ህጉን ተላልፈው የተገኙ ነጋዴዎች በመቅጣት 7 ሚሊየን 773 ሺሕ 280 ብር፣ ከተወረሱ ምርቶች ሽያጭ 1 ቢሊየን 525 ሚሊየን 687 ሺሕ 517 ብር በድምሩ 1 ቢሊየን 533 ሚሊየን 460 ሺሕ 797 ብር ለመንግስት ገቢ ማድረግ መቻሉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡