በጋምቤላ ሰላም ለማስጠበቅ የተጠናከረ የጸጥታ ማስከበር ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

ጥቅምት 25/2014 (ዋልታ) – በጋምቤላ ክልል የአሸባሪቹ ሕወሓት እና ሸኔ ተላላኪዎች የጥፋት ድርጊት እንዳይፈጽሙ በመቆጣጠር ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ የተጠናከረ የጸጥታ ማስከበር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ፖለስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ባደረገው ክትትል ለሸኔ በተላላኪነትና በግብረ አበርነት የተጠረጠሩ 17 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል።

የክልሉ ፖሊስ  ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ እንደገለፁት እራሱን “ጋነግ” በማለት የሚጠረው የሽብር ቡድኖቹ ተላላኪ በክልሉ የጸጥታ ችግር ለመፍጠር ተዳጋጋሚ ሙከራዎች እያደረገ ነው።

የሽብር ቡድኖቹ ሀገር ለማፍረስ የጀመሩትን እኩይ ሴራ በጋምቤላ ክልል በተላላኪዎች አማካኝነት የጸጥታ ችግር ሊያስፈጽሙ ስለሚችሉ ኮሚሽኑ ከሌሎች የጽጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ጠንካራ የጥበቃና የክትትል ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በተደረገው ክትትልም በጋምቤላ ከተማ የሸኔ አባል እንደሆኑ የተጠረጠሩ 10 ግለሰቦችና ለሽብር ቡድኑ ስንቅ ለማቀበል ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ሰባት ግብር አበሮችን ትናንት ምሽት በቁጥጥር ስር ማዋሉን አሰታውቀዋል።

እንደ ኮሚሽነር አቡላ ገለጻ  ክልሉ ሰፊ  የድንበር ወሰን ያለው ከመሆኑ ጋር ተይዞ የሽብር ቡድኖቹ ተላላኪ የሆኑ ሰርጎ ገቦች ወደ ክልሉ እንዳይገቡ የጸጥታ አካላት ስምራት ተደርጓል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።