መላው የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ኢትዮጵያን ከአሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ ነፃ ለማወጣት በጋራ እንዲቆም ተጠየቀ

ጥቅምት 26/2014 (ዋልታ) መላው የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመሆን ኢትዮጵያን ከአሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ ነፃ ለማወጣት በጋራ እንዲቆምና እንዲታገል የለጋጣፎ ከተማ ከንቲባ በሪሶ ተመስገን ጥሪ አቀረቡ፡፡

በመላው ኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች የሕወሓት እና ሸኔን የሽብር ቡድኖች የሚቃወም ሕዝባዊ ሰልፍ እየተካሄደ ሲሆን፤ በለገጣፎ እየተካሄደ ባለው የተቃሞ ሰልፍ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባው አሸባሪው የሕወሓት ጥፋት ቡድን ባለፉት የሥልጣን ዘመኑ መላው ኢትዮጵያዊያንን ሲጨቁንና ሲዘርፍ ነበር ሲሉ አስታውሰዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን ያበላውን ሕዝብ ክዶ ዛሬ ከውስጥ እና ከውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ብርቱ ጥረት እያደረገ ይገኛልም ብለዋል፤ እንደማይሳካለት በመጠቆም፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት ከሕወሓት ጋር አብራችሁ የኦሮሞን ሕዝብ ክዳችኋል በሚል ሲናገር የነበረው አሸባሪው ሸኔ ሕዝብን ሲዋሽ እንደነበርም ዛሬ ከሕወሓት ጋር በመጣመር በተግባር ማሳየቱን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያን ሉኣላዊነት ለማስጠበቅና የሽር ቡድኑን ለማጥፋት የሚችል ሁሉ የአገር መከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀል ወደ ግንባር መዝመት የማይችለው ደግሞ በያለበት አከባቢውን በመጠበቅ የሚችለውን ሁሉ እንዲያደርግ ተጠይቋል።
በሚልኪያስ አዱኛ (ከለገጣፎ)