የአበርገሌ ነዋሪዎች አሸባሪውን ሕወሓት በሕዝባዊ ማዕበል እየደመሰሱ ነው

ጥቅምት 26/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል የዋግና አካባቢው ነዋሪዎች ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገናቸው ጋር በመሆን በአካባቢው የገባውን ጠላት እየደመሰሱ መሆናቸውን ተናገሩ።

አሸባሪው ሕወሓት በዋግ ሕዝብ ላይ ያልፈጸመበት የበደል ዓይነት የለም የሚሉት ነዋሪዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት የሆነውን የሽብር ኃይል ዛሬም እንደትናንቱ በከፍተኛ ወኔ ተነስተው እየተፋለሙት እንደሆነ ነው የገለፁት።

የአበርገሌ፣ የፃግብጂ፣ የዳህና፣ የሳህላ ሰየምት፣ የዝቋላ፣ የሰቆጣ እና የጋዝጊብላ ወረዳ ነዋሪዎች በየአቅጣጫው እየተመመ ከሚገኘው ወገን ጋር በመሆን አሸባሪውን ኃይል እየቀጡት ነው።

እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ የአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኃይል በአሁኑ ወቅት በከበባ ውስጥ ገብቷል፡፡ ምርጫው እጅ መስጠት ወይም ባለበት ማለቅ ሊሆን እንደሚችል ነው ያብራሩት።

አሁንም ወራሪው ኃይል በቀያቸው ያሻውን እየፈጸመ መኖር ስሌለበት የመጨረሻ እስትንፋሱን ለመዝጋት በገባባቸው ቦታዎች ሁሉ ሕዝቡ በከፍተኛ ቁጣ ባገኘው መሳሪያ ሁሉ አንድም እንዳይተርፍ አድርጎ እየደመሰሰ ነው ሲሉ በዓይናቸው ያዩትን ለአሚኮ ተናግረዋል።

በዚህ ታሪካዊ ትግል መዝመት የሚችል ኢትዮጵያዊ ሁሉ በመዝመት ኢትዮጵያ ዛሬም ለጠላት የማትነካ ገናና አገር መሆኗን ለዓለም ልናሳይ ይገባናል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡