የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የ12ኛ ክፍል ፈተና በ2ኛ ዙር ይሰጣል

ጥቅምት 27/2014 (ዋልታ) የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በ2ኛ ዙር እንደሚሰጥ የአገር ዐቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተፈራ ፈይሳ እንደገለፁት ከ600 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ከ2 ሺሕ በላይ በሆኑ የፈተና ጣቢያዎች ለመፈተን ተመዝግበዋል።

በሁለት ዙር ፈተናው እንደሚሰጥ የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከ90 በመቶ በላይ ተፈታኞች በመጀመሪያው ዙር ፈተናቸውን እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

የጸጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች 2ኛው ዙር ፈተና እንደሚሰጥ መጠቆማቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

2ኛው ዙር ፈተና ከሚሰጥባቸው ቦታዎች መካከል ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ እና ዋግኽምራ ዞኖች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

“በሁለተኛው ዙር ፈተና የሚወሥዱ ተማሪዎች የሥነ ልቦና ግንባታና ክለሣ ተደርጎ ፈተና ይወሥዳሉ” ብለዋል።

በአማራ ክልል ከተለዩ ቦታዎች ውጪ በሌሎች አካባቢዎችም የሚለዩ ቦታዎች ካሉ በ2ኛው ዙር ፈተናውን እንደሚወስዱ ገልጸዋል።