ትናንት ሴት ልጅ የተገላገለችው ተማሪ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እየወሰደች ነው

ጥቅምት 29/2014 (ዋልታ) ትናንት ሴት ልጅ የተገላገለችው የሸዋሮቢት አጠቃላይ 2ኛ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳራ ሽመልስ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እየወሰደች ነው።

በአማራ ክልል ሸዋሮቢት ከተማ የሸዋሮቢት አጠቃላይ 2ኛ መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እየተሰጠ ሲሆን በትምህርት ቤቱ 775 መደበኛና 11 የግል ተፈታኞች ብሄራዊ ፈተናውን እየወሰዱ  ይገኛሉ።

ከትምህርት ቤቱ ተፈታኞች መካከል በትናንትናው ዕለት ሴት ልጅ የተገላገለችው ተማሪ ሳራ ሽመልስ ትገኛለች። ተማሪ ሳራ በጥሩ ጤንነት ላይ ሆና በዛሬው እለት ፈተናውን እየወሰደች እንደሆነ መግለጿን ኢዜአ ዘግቧል።

የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎችም ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ በመሰጠት ላይ ይገኛል።