የህልውና ዘመቻውን የሚደግፍና ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም ሰልፍ በዲሲ ተካሄደ

ጥቅምት 30/2014 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የህልውና ዘመቻ የሚደግፍና የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በዋሽንግተን ዲሲ ተካሂዷል።

“በሃገር ህልውና እና አንድነት አንደራደርም” በሚል መሪ ቃል ነው ሰላማዊ ሰልፉ የተካሄደው።

በነጩ ቤተ መንግስት ፊት ለፊት በተካሄደው በዚህ ሰልፍ አሜሪካ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አክብሪ፣ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ጣልቃ ገብነት ታቁም፣ ኢትዮጵያ በራሷ ጉዳይ የሌሎችን ትዕዛዝ አትቀበልም፣ “ኢትዮጵያን ከአጎዋ የማስወጣት ውሳኔ ስህተት ነው፤ የሚጎዳው ንጹሃን ዜጎችን ነው የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ አሸናፊ የሆነችው በአጎዋ ሳይሆን በአድዋ ነው፣ ሲ ኤንኤን በኢትዮጵያ ላይ የሚሰራውን ሀሰተኛ መረጃ ያቁም፣ ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢዎችን አሸንፋለች አሁን ኒዮ-ኮሎኒያሊስቶችንም ታሸንፋለች” የሚሉ ሃሳቦች ተስተጋብተዋል።

በሰልፉ ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶችና ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እየተሳተፉ ሲሆን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ህወሕት በፈጸመው ጥቃት በግፍ የተጨፈጨፉ የአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት የሚዘክር መርሃ ግብርም ተካሂዷል።

ሠልፈኞቹ የአገርን ሕልውና ለማስጠበቅ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ሌሎች የጸጥታ አካላት አጋርነታቸውንና ድጋፋቸውን አሳይተዋል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ያልተገባ ጫና እና ጣልቃ ገብነት እንድታቆምና የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን እንድታጤን የሚያሳስቡ መልዕክቶችም ተላልፈዋል።

ሰላማዊ ሠልፉ በሠላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ግብረ ሃይል በዲሲ እና በአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና የተለያዩ ተቋማት ትብብር የተዘጋጀ መሆኑን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።