የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ከዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

ጥቅምት 30/2014 (ዋልታ) የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ከዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዑስማን ዲዮን ጋር ተወያዩ።

ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ ያሉትን 1 ሺሕ 600 ያህል የቴክኒከና ሙያ ተቋማት ብቁ ማድረግ፣ የሥራ ፈጠራ ሃሳብን ከትምህርት ሥርዓት ጋር ማገናኝት፣ ዕውቀትና ቴክኖሎጂን ማሸጋገር፣ ግብርና እና ቱሪዝምን በመሰሉ እና ብዙ ሰዎችን ሊያካትቱ በሚችሉ የሥራ ዘርፎች ላይ ማተኮር እንዲሁም ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ወደ ሥራ መለወጥ የወደፊት አቅጣጫችን ነው ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ዑስማን ዲዮን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ብዙ ወጣቶች የሚገኙባት አገር እንደመሆኗ መጠን ያላትን ሀብት በመጠቀም እንደግብርና እና ቱሪዝም በመሳሰሉት ዘርፎች ላይ ጠንክሮ በመሥራት በክህሎት ብቁ የሆኑ ወጣቶችን ወደ ሥራ ማሰማራት አለባት ብለዋል፡፡

የተለያዩ አገራትን የቴክኒክና ሙያ እንዲሁም የሥራ ተሞክሮ በማንሳት እና በኢትዮጵያ ሥራና ክህሎትን በተመለከተ የሚታዩ ክፍተቶች ላይ ከተወያዩ በኋላ የዓለም ባንክ በቴክኒክና ሙያም ሆነ ሥራን በተመለከተ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ዑስማን ዲዮን እና ቡድናቸው ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ያደረጉትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አድንቀው በቀጣይም በጋራ ለመስራት ላሳዩት ተነሳሽነት ምስጋና ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡