በህዳር ወር ነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በነበረበት እንደሚቀጥል ተገለጸ

ኅዳር 1/2014 (ዋልታ) በህዳር ወር ሁሉም የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥቅምት ወር ሲሸጥበት በነበረው ዋጋ እንደሚቀጥል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ የአውሮፕላን ነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ የዓለም ነዳጅ ዋጋን መሰረት በማድረግ በጥቅምት ወር 1 ሊትር ሲሸጥበት ከነበረው 47 ብር ከ43 ሳንቲም ላይ የዋጋ ማሻሻያ እንደተደረገበት ገልጿል፡፡

በዚህም መሰረት በህዳር ወር የ1 ሊትር የአውሮፕላን የነዳጅ ችርቻሮ መሸጫ ዋጋ 58 ብር ከ77 ሳንቲም መሆኑን አመልክቷል።

በቀጣይ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የዓለም የነዳጅ የገበያ ዋጋን መነሻ በማድረግ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

የዓለም የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ በየወሩ በመጨመር ላይ ቢገኝም መንግሥት የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በተረጋጋ ሁኔታ ለማስቀጠል ሲል በነበረበት ዋጋ እንዲቀጥል ማድረጉን መግለጫው አመላክቷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት መስከረም 23 ቀን 2001 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የነዳጅ ምርቶች ዋጋ በየወሩ እንዲከለስ መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል።