የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ሦስት ትዕዛዞችን አስተላለፈ

ኅዳር 2/2014 (ዋልታ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ እየተገኙ ያሉ ድሎችን አፅንቶ መቀጠል እንዲቻል ሦስት ትእዛዞችን አስተላለፈ።

ዕዙ የጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ እንቅስቃሴ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌዎችን በማስፈጸም ባለፉት ቀናት አኩሪ ውጤቶችን አስመዝግቧል፣ ሕገ ወጦችን በቁጥጥር ሥር አውሏል፣ በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችም ተይዘዋል ብሏል።

ይህ ያስደነገጠው ጠላት የጸጥታ አካላትን መልካም ስም ለማጥፋት፣ ለማሸማቀቅና ሥራቸውን በሙሉ ዐቅም እንዳይሠሩ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ያለው የዕዙ መግለጫ በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ አጋጣሚ ለመጠቀም የሚፈልጉ ጥቂት የጸጥታ አካላት መኖራቸውን ዕዙ አረጋግጧል፤ በእነዚህ አካላት ላይም በጠራ መረጃ ላይ በመመሥረት የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ ትእዛዝ ሰጥቷል።

የጸጥታ ኃይሎች ለሕዝቡ ደኅንነት ሥጋት የሚሆኑትን ለመመንጠር ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲያግዝ ማንኛውም ቤት አከራይ የተከራይን ማንነት የሚገልጽ ሙሉ መረጃ ይህ መግለጫ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ፣ በአቅራቢያው በሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ እንዲያስመዘገብም ታዟል።

ይህን በማያደርጉት ላይ አስፈላጊው ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ ነው ትእዛዝ የተላለፈው።

ሕገወጥ ግለሰቦች ብሔራዊ ባንክ ካወጣቸው ደንቦችና የአፈፃፀም መመሪያዎች፣ እንዲሁም ከባንኮች ሕጋዊ አሰራር ውጭ፣ በተጭበረበረ መንገድ የገንዘብ ዝውውር እያካሄዱ መሆኑ ተደርሶበታል፤ ለዚህም በጊዜው ተገቢው እርምጃ ተወስዷል ብሏል።

በመሆኑም  ቀደም ብለው ከወጡ ሕጎችና መመሪዎች ውጭ ሲሰሩ በሚገኙት ባንኮች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሠረት በማድረግ  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሕግ አስፈፃሚ አካላት ጋር በመቀናጀት ጥብቅ እርምጃ እንዲወስድ ታዟል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ማንኛውም የተጭበረበረ የገንዘብ ማዘዋወሪያ ሰነድ ይዘው በተገኙ ላይ ከወትሮው በተለየ ጥብቅ ርምጃ እንዲወሰድም ትዕዛዝ መሰጠቱን ዕዙ ባወጣወ መግለጫ አስጠንቅቋል።