በመዲናዋ ዕጣ የወጣባቸውን 68 ሺሕ ቤቶች ለማስረከብ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ኅዳር 3/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ዕጣ የወጣባቸውን 68 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለዕድለኞች ለማስረከብ እየሰራ መሆኑን ገለፀ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ሽመልስ ታምራት በመዲናዋ ዕጣ ወጥቶባቸው ለዕድለኞች ያልተላለፉ 68 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስረከብ እየተከናወነ ስላለው ተግባር ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በተያዘው በጀት ዓመት 139 ሺሕ ቤቶችን በመገንባት ላይ እንደሆነና ቤቶቹ በተለያየ የግንባታ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ከቤቶቹ ግንባታ በተጨማሪ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች እንዲሟላላቸው ከሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ያስሚን ወሀብረቢ በበኩላቸው አስተዳደሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን በሽርክና፣ በመንግሥትና በግል አጋርነት እያስገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
በመንግስት ከሚገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ ከ12 ሺሕ በላይ ዜጎች በማሕበር እንዲደራጁ በማድረግ የቤት ባለቤት የሚሆኑበትን አማራጭ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንን ከቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።