መንግሥት የሮይተርስን ሃሰተኛ መረጃ ኮነነ

ኅዳር 3/2014 (ዋልታ) ሮይተርስ “በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የብሔር ማንነትን የሚገልፅ መታወቂያ ግዴታ መያዝ ሆኗል” ሲል ያሰራጨውን ሃሰተኛ ዘገባ መንግሥት ተቃወመ።
ሮይተርስ “በኢትዮጵያ የብሔር ማንነትን የሚገልፅ መታወቂያ ግዴታ ሆኗል” ሲል ሃሰተኛ ዘገባ ማሰራጨቱን ዋልታ ጧት መዘገቡ ይታወሳል።
ይህንኑ በተመለከተ መግለጫ ያወጣው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኢትዮጵያ በመታወቂያ ካርድ ላይ የብሔር ማንነትን ለማስወገድ በወሰነችበትና እየተገበረች ባለችበት ወቅት ሮይተርስ በዚህ መልኩ መዘገቡን ኮንኗል።
ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት አሸባሪው ሕወሐት ሲተገብረው የነበረውን የብሔር ማንነትን የሚገልጸውን የመታወቂያ ካርድ ለመተካት እየሰራ መሆኑ የሚታወቅ ነው ብሏል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዜጎች ማንነታቸውን የሚገልፅ የነዋሪነት መታወቂያ ወይም እንደ መንጃ ፍቃድ ፓስፖርትና ሌሎች ተመጣጣኝ የሆኑ መለያዎችን እንዲይዙ እንጂ ብሔር የሚገልጽ መታወቂያ ያዙ የሚል መግለጫን አልሰጠም፤ እንዲህ ያለ አሰራርም አልተከተለም።
ሮይተርስ አገር ለማፍረስ የሚጣመሩ ስብስቦችን በቀጥታ ስርጭት ሽፋን መስጠትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የሆነ የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ዘመቻን እያደረገ ነው።