አሸባሪው ሕወሓት በአማራ ክልል ቢያንስ 184 ንፁሃንን ገድሏል

ኅዳር 4/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት በወረራ በያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ከሰኔ እስከ ነሐሴ መጨረሻ ቢያንስ 184 ንፁሃንን እንደገደለ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
ኢሰመኮ ከሐምሌ 2013 ጀምሮ በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት ወደ አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ በአሸባሪው ሕወሓት ኃይሎች የተፈጸሙ የሰብኣዊ መብት እና የሰብኣዊነት ሕግ ጥሰቶችን በተመለከተ ያደረገውን ምርመራ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።
በሪፖርቱም በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር እና በሰሜን ወሎ ዞኖች በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች የመልሶ መቋቋሚያ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አመላክቷል።
የተፈጸሙ ጥሰቶች የጦር ወንጀል ስለመሆናቸው አመላካች ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጾ፤ ከሰኔ 21 እስከ ነሃሴ 22/2013 ባለው ጊዜ በቡድኑ የተፈጸሙ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን ማጣራቱን ገልጿል።
“ምርመራው ባተኮረባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች በተደረገው ጦርነት ቢያንስ የ184 ንፁሃን ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ እንዲሁም በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት እና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል” ብሏል።
በተለይ የሕወሓት ታጣቂዎች በቁጥጥራቸው ስር በገቡ ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች ሲቪል ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውንና ማቁሰላቸውን፣ ሰፊ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት ሆን ብለው መፈፀማቸውን እንዳረጋገጠ ይፋ አድርጓል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) “የተደረገው ምርመራ ሪፖርት ግኝቶች በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በአፋጣኝ ማስቆም እንደሚገባ የሚያመላክት ነው” ብለዋል።