ሕወሓት የሁሉም ኢትዮጵያዊ የህልውና ስጋት ነው ሲሉ አምባሳደር ፍፁም አረጋ ገለፁ

ኅዳር 4/2014 (ዋልታ) – አሸባሪው ሕወሓት የኢትዮጵያዊያን የኅልውና ስጋት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በጋራ ለመከላከል በእልህ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለፁ።

አምባሳደሩ በዋሽንግተን ከስፑትኒክ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የደኅንነት ስጋት የፈጠሩትን የአሸባሪው ሕወሓት መሪዎች ለፍትሕ ለማቅረብ እየተሰራ ነው።

በውይይትና በድርድር ስም እነዚህ ግለሰቦች ከፍትሕ እንዲያመልጡና አሸባሪው ድርጅትም ትንፋሽ አግኝቶ ራሱን ይበልጥ እንዲያጠናክር የሚደረገውን ሙከራ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለጥቂት ስግብግብ ግለሰቦች ሲባል በርካታ የትግራይ ነዋሪዎች በግዳጅ የጦርነቱ ተዋናይ በመሆናቸው ጉዳቱን ከባድ እንዳደረገው ገልጸዋል።

“አሸባሪው ሕወሓት ከጥቂት አምባገነን ግለሰቦች በስተቀር በየትኛውም መስፈርት የትግራይን ሕዝብን ይወክላል ብለን አናምንም” ያሉት አምባሳደሩ ድርጅቱ እምነት የማይጣልበትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት እንደማይፈልግ በተደጋጋሚ ለዓለም ማሳወቁንም አስታውሰዋል።