የኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት ለአጠቃላይ ቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ ነው – እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

ኅዳር 6/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት ለአጠቃላይ የቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) አመለከቱ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ከህንዱ ዲዲ ሚድያ ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ “አሸባሪው ሕወሓትን ለመደገፍ ለሚሞክሩ ኃይሎች የማረጋግጠው ኢትዮጵያ እንደምታሸንፍ ነው” ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

አሸባሪው ሕወሓትን የውክልና ጦርነት ለማድረግና ለመደገፍ ለሚሞክሩ ኃይሎችም ግልፅ መልእክት አስተላልፈዋል።

አሸባሪው ቡድን ከውጭ ባሉ ኃይሎች የሳተላይት እና ሌሎችም ድጋፎች እንደሚያገኝ መንግስት በትክክለኛ ማስረጃ ማረጋገጡን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው የኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት ለአጠቃላይ የቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

አሸባሪው ሕወሓት ባለፉት 27 ዓመታት የፌዴራል ሥርዓቱን በተሳሳተ መንገድ በመጠቀም የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት በተጠና መልኩ ሲጥስ እንደነበር ያስታወሱት ኢዮብ (ዶ/ር) አሁን ላይ በኢትዮጵያ የተፈጠረው ግጭት የሽብር ቡድኑ በሀገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለመቀልበስ በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ መሆኑን አስረድተዋል፡፡