አፍሪካዊያን ወደ ዳግም ቅኝ ግዛት እንዳይመለሱ ከኢትዮጵያ ጎን ሆነው እንዲታገሉ የፓን አፍሪካ አቀንቃኙ ማፖንጋ ጆሹዋ ጠየቁ

ማፖንጋ ጆሹዋ

ኅዳር 6/2014 (ዋልታ) የአፍሪካ የነፃነት እናት የሆነችው ኢትዮጵያ በበረከተባት ጫና ብትዳከም አፍሪካ ያለጥርጥር ወደ ዳግም ቅኝ ግዛት ትገባለች ሲሉ የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ፣ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪው ማፖንጋ ጆሽዋ 3ኛ ገለፁ።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የነፃነት ምልክት ነች ያሉት የታሪክ ተመራማሪው ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ጦርነት ጀርባ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት እንዳለበትም ያሰምራሉ፡፡

ጦርነቱ ኢትዮጵያ ላይ ቅኝ የመግዛት ፍላጎት ባላቸው አካላት እንደተከፈተ በማንሳትም አፍሪካዊያን አንድነታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋለው የጣልቃ ገብነት ችግር የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ችግር በመሆኑ አፍሪካዊያን ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ብለዋል፡፡

ከኦቢኤን አፍሪካ ፊውቸር የተሰኘ መርሃግብር ጋር ቆይታ ያደረጉት ጆሽዋ በአሜሪካ መሪነት ኢትዮጵያን ወደ ትንንሽ አገራት ለመከፋፈል በምዕራባዊያኑ የተሸረበውን ሴራ መታገልና የአፍሪካን በራስ የመወሰን አቅም ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡