የኢፌዴሪ አየር ኃይል በኤር ፖሊስ ኮማንዶ ያሰለጠናቸውን የሰራዊት አባላት አስመረቀ

ኅዳር 6/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ አየር ኃይል በመጀመሪያ ዙር በኤር ፖሊስ ኮማንዶ ያሰለጠናቸውን የሰራዊት አባላት አስመረቀ፡፡
የአየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአየር ሎጀስቲክስ ብ/ጄ ነገራ ሌሊሳ በጀግናው ሰራዊታችንና በህዝባችን መስዋዕትነት የተደቀነብን የህልውና አደጋ እየተቀለበሰ ይገኛል ብለዋል።
አየር ኃይል ለምድር ኃይላችን አስተማማኝ የውጊያ ድጋፍ ከመስጠት ባለፈ የጠላት ወረዳ ድረስ ዘልቆ በመግባት አሸባሪ ቡድኑ ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ የገለፁት ጄነራል መኮንኑ ተመራቂ የኤር ፖሊስ ኮማንዶ የሰራዊት አባላትም ለተቋሙ የግዳጅ አፈፃፀም ስኬታማነት ተጨማሪ አቅም በመሆናችሁ ለቀጣይ ተልዕኮ ራሳችሁን ይበልጥ በማዘጋጀት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የስልጠናው አስተባባሪ ኮ/ል ተፈራ እሸቴ በበኩላቸው ሰልጠኞች የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚያስችል ስልጠና በመውሰድ በላቀ ውጤት ማጠናቀቅ መቻላቸውን መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
ከተመራቂዎች መካከል አንዳንዶች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ወደፊት የሚሰጠንን ማንኛውም ግዳጅ በፅናትና በቁርጠኝነት እንድንወጣ አጋዥ ነው ብለዋል።