ኅዳር 6/2014 (ዋልታ) “ለአሜሪካ መንግስት ግልፅ መልእክት ማስተላለፍ የምንፈልገው የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል በሰሜኑ ግጭት ጣልቃ እንዲገባም ሆነ ኃይል ሊያሰፍር አይገባም” ሲል የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት አስገነዘበ።
ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ ለአሜሪካን ኮንግረስ፣ ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ እና ለአሜሪካ መከላከያ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ እንደማይገባ አስገንዝቧል።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሁለት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የመከላከያ መሪዎች በኢትዮጵያ ባለው የሰሜኑ ግጭት አሜሪካ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን ልታካሂድ ትችላለች ማለታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት ሊቀ መንበርና ተባባሪ መስራች ዲያቆን ዮሴፍ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
በትግራይ ያለው ግጭት የውስጥ ጉዳይ ሆኖ በኢትዮጵያውያን እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጠው መንግስታቸው ብቻ ሊያዝ እንደሚገባ አመላክተዋል።
“ኢትዮጵያ አሜሪካውያንን ወክለን እንደምንናገረው የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ከማባባስ እንዲቆጠብ እንጠይቃለን” ያለው መግለጫው የአሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ኃላፊነት የጎደለውና የተሳሳተ ውሳኔ ነው ብሏል፡፡
ይህም አሜሪካ ለ20 ዓመታት በአፍጋኒስታን በነበራት ቆይታ በመጨረሻዎቹ ዓመታት ተፈጥሮ የነበረውን ቀውስ ማንም የሚያስታውሰው ነው፤ አብዛኞቹ አሜሪካውያንም ይህን ድርጊት ተቃውመውታል ሲል መግለጫው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ይልቁንም የኢትዮጵያን ሉአላዊነት፣ የግዛት አንድነትና ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን የሚያጠናክር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንዲተገብር ምክር ቤቱ ጠይቋል፡፡
ሚዛናዊ የሆነ አቀራረብ በሌለበት ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን ከማይጋፉ ኃይሎች ጋር ጥምረት ለመፍጠር ትገደዳለች፤ በኢትዮጵያ የሚደረግ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለማያባራ ቀጣናዊ የፖለቲካዊ ቀውስ ይዳርጋል፤ ይህም ቀጣናውና የዓለም ደህንነትን በማናጋት ጭምር ቀውሱን ያባብሳል ተብሏል፡፡
ምክር ቤቱ የኢትጵያና የአሜሪካውያን ወታደራዊ ጥምረት ለብሄራዊ ደህንነት ያለውን ፋይዳ ይረዳል እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ያላቸውን ፋይዳ ይገነዘባል፤ በዚሁ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ዜጎች ለአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት የከፈሉትን ዋጋም ማንሳት አስፈላጊ ነው ሲል መግለጫው አመላክቷል፡፡
አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተሰሚነት ለማስቀጠል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን 118 ዓመታት ያስቆጠረ ግንኙነት ዳግም የምታጤንበት ወቅት መሆኑን የጠቆመው ምክር ቤቱ ይህን አላማ ማስቀጠል የሚቻለውም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን በመከባበርና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ በማተኮር እንደሆነ አመልክቷል።