ጀግንነታችን እና የአባቶቻችን ታሪክ ባለቤትነት የሚፈተሽበት ጊዜ ነው – ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ

ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

ኅዳር 8/2014 (ዋልታ) “ወቅቱ ጀግንነታችን እና የአባቶቻችን ታሪክ ባለቤትነት የሚፈተሽበት ነው” ሲሉ የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በቡሬ ከተማ እየተካሄደ ባለው የምዕራብ ጎጃም ዞን ህዝባዊ ኮንፈረንስ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በጀግኖች የታፈረች እና የታደለች ሀገር ናት፤ ሆኖም ሁልጊዜ ይህን ጀግንነት ማውሳት ብቻ በቂ አይሆንም ብለዋል።

ወራሪውን የሕወሓት ኃይል በመደምሰስ በአንድነትና በመስዋዕትነት ኅልውናችንን የምናስቀጥልበት ወቅት መሆኑንም ነው የገለፁት።

አሸባሪውን እየተፋለመ ያለው ኃይል ፅናት ያለው የማይቋረጥ ተተኪ እና የማይነጥፍ ደጀን ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋልም ብለዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪው መልካሙ ተሾመ በበኩላቸው ነፃነት በመስዋዕትነት እና በተግባር ፍልሚያ የሚገኝ ነው፤ በመሆኑም የዞኑ ህዝብ ከመላ ኢትዮጵያውያን ጋር በመቆም ጠላትን ለመደምሠስ ዝግጁ እንደሆነ እምነታቸው መሆኑን ልጸዋል።

በአርበኝነት ተጋድሎ የሀገርን ኅልውና ለማስቀጠል በሚደረገው ትግል የምዕራብ ጎጃም ህዝብ ከፊት በመሠለፍ ወራሪውን ድል በማድረግ የሀገሩን ልዕልና ያረጋግጣል ብለዋል።

በመርኃግብሩ የመወያያ ዕሁፍ ቀርቦ ምክክር የሚደረግ ሲሆን ለኅልውና ዘመቻው የዞኑን ተሳትፎ የሚያሳድጉ ውሳኔዎች ይጠበቃሉ።

በመር ሀግብሩ ከ5 ሺህ በላይ ከዞኑ ሁሉም ወረዳና ቀበሌዎች የተወከሉ የህብረተሠብ ክፍሎች መታደማቸውን የኢቢኮ ዘገባ ያመለክታል።