አሸባሪውን ቡድን መደገፍ ወንጀልና ወንጀለኛን ማበረታታት መሆኑን ኑሯቸውን በእንግሊዝ ሀገር ያደረጉ ምሁር ገለጹ

ዶክተር ጀማል ገምታ

ኅዳር 8/2014 (ዋልታ) አንዳንድ ምዕራባውያን አሸባሪውን ሕወሓት ሲደግፉ ወንጀልና ወንጀለኛን ማበረታታት መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ሲሉ ኑሯቸውን በእንግሊዝ ሀገር ያደረጉ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛና የህክምና ባለሙያ ዶክተር ጀማል ገምታ ገለጹ።

ባለሙያው አንዳንድ ምዕራባውያንና ደጋፊዎቻቸው የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በውል ሳይገነዘቡ ሀገር ለማፍረስ ቀን ከሌሊት ከሚተጋው አሸባሪ ሕወሓት ጎን መሰለፋቸውን ገልጸዋል።

ከኦቢኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት ዶክተር ጀማል በቀድሞ የወያኔ አገዛዝ በሁርሶ ማጎሪያ ኦነግ ተብለው ለሰባት ዓመታት እንደታሰሩና ከሀገራቸው በግፍ መገፋታቸውን ገልጸው ወያኔ ዓለም ያወቀው ወንጀለኛ መሆኑን በራሴ እስር ቤት በግፍ አጉሮ ባደረሰብኝ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት አንዱ ህያው ምስክር ነኝ ብለዋል።

ሰላምና ኢ-ፍትሃዊነት ልክ “እንደ ቀንና ሌሊት ነው” የሚሉት ዶክተር ጀማል ከሕወሓት ጋር መኖር ከወንጀለኛ ጋር መኖር ነውና ይህ እንደምን ይቻላል? ሲሉ ደግመው ይጠይቃሉ።

እናም ምዕራባውያን ወንጀለኛን መደገፋቸውና ማበረታታቸው ወንጀሉን መደገፋቸውንና ከኢ-ፍትሃዊነት መወገናቸውን ያሳያል ብለዋል።

ዶክተር ጀማል አክለውም ከዚህ አሸባሪ ቡድን ጋር ቆመናል የሚሉት እንደ አሸባሪ ሸኔ ያሉ ተላላኪዎቹ ለግል ጥቅምና ለተላላኪነት ባህላቸው እንጂ ለኦሮሞ ህዝብ አስበው እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በመሆኑም ወንጀለኛን የሚገባውን ቅጣት በመስጠት የሀገርን ሉዓላዊነት ማስቀጠል የሁሉም ሰላም ወዳድ ግዴታ ነው ብለዋል።