ሀገርን ከጥፋት ኃይሎች ለመታደግ መዘጋጀታቸውን የብርሸለቆ ምልምል ሰልጣኞች ገለጹ

የብርሸለቆ ምልምል ሰልጣኞች

ኅዳር 9/2014 (ዋልታ) የምዕራብ ዕዝ ሙዚቃ እና ቴአትር ቡድን በብርሸለቆ መሰረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለ35ኛ ዙር ምልምል ሰልጣኞች የመድረክ ስራዎችን አቅርቧል፡፡

የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ዋና አዘዥ ኮ/ል ጌታቸው አሊ “ከአራቱም የሃገራችን ማዕዘናት ሆ ብሎ ወደ ማሰልጠኛ ማዕከላችን የተመመውን የቁርጥ ቀን ልጅ ልታበረታቱ፣ ልታዝናኑ እና ሃገራዊ ፍቅሩን ይበልጥ ልታጎለብቱ የኪነ-ጥበብ ድግስ አዘጋጅታችሁ በመካከላችን ስለተገኛችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው” ብለዋል::

የምዕራብ ዕዝ ሙዚቃ እና ቴአትር ቡድን አስተባባሪ ሌ/ኮሎኔል ጥላሁን በቀለ በበኩላቸው ኪነ-ጥበብ በሰላም ጊዜ ለሃገር እድገት ትልቅ ሚና እንዳለው ሁሉ በጦርነት ወቅት ወኔን፣ ቆራጥነትን፣ የስነ-ልቦና ዝግጁነትን የሚቀሰቅስ የጦር መሳሪያ በመሆኑ ሀገራችን ያጋጠማትን ወራሪ ኃይል ለመቀልበስ በተለያዩ ቦታዎች ቅስቀሳ በማድረግ የበኩላችንን ድርሻ እየተወጣን እንገኛለን ብለዋል::

በትምህርት ቤቱ ስልጠናቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ምልምል ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት የዕዙ ሙዚቃና ቴአትር ቡድን ሠራዊታችን ያለበት ቦታ ድረስ በመገኘት የተለያዩ ሞራል ቀስቃሽ የሆኑ ሃገራዊ ጣዕመ ዜማዎችን በማቅረባቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡

የሚሰጣቸውን ወታደራዊ ስልጠና በብቃት በመወጣት ሃገርን ከጥፋት ኃይሎች ለማዳን ዝግጁ መሆናቸውን መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል::